ቀጥታ፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ያደረግነው ውይይት ለሀገር የሚጠቅምና ዘመኑን የዋጀ ምሁርነትን እንድናጠናክር መነሳሳትን የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2018(ኢዜአ)፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር ያደረግነው ውይይት ሀገርን የሚጠቅም፣ ዘመኑን የዋጀና ንድፈ ሐሳብን ከተግባር ጋር ያስተሳሰረ የምሁርነት ሚናችንን እንድናጠናክር መነሳሳትን የፈጠረ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

ምሁራን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሀገር ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጽሑፍ በማቅረብ ከምሁራን ጋር ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።


 

ውይይቱን አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን፤ መድረኩ መንግሥት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይና የምሁራንን ሚና ዳግም የፈተሸ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም በሰጡት አስተያየት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የተደረገው ውይይት በሀገር ዕድገት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሳይንስ ዙሪያ የምሁራንን ድርሻ በዝርዝር የዳሰሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምሁር ማኅበረሰብና ሀገርን የማገልገል ግዴታ እንዳለበት የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ የምርምር ሥራዎችም ችግር ፈቺና ለሕዝብ የሚጠቅሙ እንዲሁም በተግባር የሚፈጸሙ መሆን እንዳለባቸው የጋራ ግንዛቤ የፈጠርንበት ነው ብለዋል።

የሀገርን ዘላቂ ዕድገት ለማረጋገጥ የመንግሥት፣ የምሁራንና የሕዝብ ቅንጅት ወሳኝ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጽጌ፤ የዳበረ የውይይት ባህል መኖር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መነሻ እንደሚሆን ገልጸዋል።


 

ፕሮፌሰር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የነበረው የውይይት መድረክ መንግሥት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰጠው ትኩረት በተግባር የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

ምሁራን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በፍጥነት መራመድና ንድፈ-ሐሳብን ከተግባር ጋር በማቆራኘት ለማኅበረሰቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት አቅጣጫ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።


 

በተመሳሳይ ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድሙ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የተደረገው ውይይት ፍሬያማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ምሁራን ዘመኑን መዋጀት እንዳለባቸው የቀረበው ሐሳብ ገንቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ልቆ መሄዱን ጠቅሰው፤ ውይይቱም የዲጂታል ዕድገትን ታሳቢ ያደረገ ዝግጁነት ወሳኝ መሆኑን ያስገነዘበ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን ራሳቸውን ማዘጋጀትና ከመማር ማስተማር ሥራ ባለፈ ከአርሶ አደሩና ከአርብቶ አደሩ ጋር ተቀራርበው መሥራት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሀሳብም መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።


 

ፕሮፌሰር የዓለምጸሐይ መኮንን በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለምሁራንና ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት መስጠታቸውን በማብራሪያቸው ተገንዝበናል ነው ያሉት።

ምሁራን ከዓለም ጋር እኩል መራመድ የሚችል ትውልድ የማፍራት ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የምሁራን ሚና ማኅበረሰቡን በሁሉም ዘርፍ ማገልገል መሆኑን በመረዳት፣ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ለሀገር ዕድገት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የተደረገው ውይይትም ምሁራን በምርምር ሥራዎቻቸው ሀገራዊ ችግሮችን የመፍታትና የሰለጠነ የሰው ኃይል የማፍራት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም