ቀጥታ፡

የገና ጨዋታ በቤተ ጉራጌዎች 

በእንዳልካቸው ደሳለኝ - ኢዜአ ወልቂጤ ቅርንጫፍ 

የገና በዓል በጉራጌዎች ዘንድ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ያለው ባህላዊ አንድምታ የተለየ ያደርገዋል። ገና በጉራጌዎች ዘንድ የልጆችና የወጣቶች ልዩ የደስታና የነፃነት ማንፀባረቂያም ነው። በዚህም ከሃይማኖታዊ መገለጫው ባለፈ ገና በጉራጌዎች ዘንድ ያለምንም እምነት ገደብ በጉጉት ይጠበቃል። 

ባህላዊ የገና ጨዋታ በተለይም በሞህር አክሊል፣ በሶዶና በደቡብ ሶዶ ወረዳዎች በስፋት እና በድምቀት ከሚዘወተርባቸው አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳሉ። በተጠቀሱት አካባቢዎችም የገና ጨዋታ ከህዳር 12 ጀምሮ እስከ ገና ማግስት ለሚዘልቅ ጊዜ ይካሄዳል።

የገና መጫወቻ ቆልማማ እንጨት በጉራጊኛ ''ድቤ'' ሲባል እንደ ኳስ ሚመታውና ከአስታ ግንድ ስር ተጠርቦ የሚዘጋጀው ሩር ''ቁየ'' ወይም ''አንቃት'' ተብሎ ይጠራል። አሁን አሁን ግን ሩሩን ወይም ''ቁየው''ን በቃጫ ኳስ ጠፍሮ በማበጀት መጫወት እየተለመደ መጥቷል። የገና ጨዋታውም በበዓሉ ዋዜማ ቀን ከሰአት በኋላ ማታ ደግሞ በጨረቃ ጭምር ይካሄዳል። 

ወጣቶች የዛሬ ዓመት ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው በተለያዩበት ቤት በመሰባሰብ በዓሉን ማክበር በአካባቢው የተለመደ ነው። ወጣቶቹ ወደሚሰባሰቡበት ቤት ሲመጡ ከባቄላ ጋር ተደባልቆ የተዘጋጀ ቆሎ ከየቤታቸው በጉራጊኛ ''ሟነ'' ተብሎ በሚጠራና ከጨርቅ በሚዘጋጅ ከረጢት ይዘው ይመጣሉ። ዕለቱም የልጆች ቆሎ ቀን ይባላል።

ከዚያም ወደ ውጭ በመውጣት በመስክ ላይ ቀኑ ሙሉ የገና ጨዋታን ሲጫወቱ ይውላሉ። ደስታው ልዩ ነው። የገና ጨዋታ ላይ ጥበብ ሞገሷን ታገኛለች።


 

ተሳታፊዎች እርስ በርስ የሚለዋወጡት የቃል ግጥም ይደመጣል። ወደ መንደራቸው ይዘው የሚነጉዱት ይወዳደሳሉ፤ በተለይም በጨዋታው የተሸነፈው ቡድን በአሸናፊዎች ይተረባል፤ አሸናፊዎች ደግሞ ያገኙትን ድል የሚያወድሱ ስንኞችን ይደረድራሉ፡፡

በገና ጨዋታ ላይ የሚገጠሙ ግጥሞች ታዲያ እንደ መዝናኛና እንደ ጨዋታ ማድመቂያ ነው የሚቆጠሩት። በዚህም ጊዜ ወጣቶቹ የገና መጫወቻ ድቤያቸውን በትከሻቸው ትይዩ ወደ ላይ ሰድረው፣ በሶምሶማ እየሮጡ፤

" ለበሞ ለበሞ

 ምድር ሰሜ ኸበሞ! /አውራጁ/

ተቀባዮች ደግሞ ዘሪቶ ለበሞ ያሆያሆ ይላሉ። ይቀጥላሉ 

በገናንዳ ቤቶ...አውንደም ሽወቶ

ቡርህማ ይስመቶ! "እየተባለ ወደ ጨዋታው ጅማሬ ይገባል።

አደረጃጀቱም በሰፈር ተቧድነው ግጥሚያ በማድረግ ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ከቀኝ ወደ ግራ ከያዘ፣ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ያለውን ስፍራ ይይዛል። አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ ''ቢል'' ‹‹ሚናህን ለይ›› ይባላል። ካስፈለገም በዱላ ቸብ ተደርጎ፣ ቦታውን እንዲይዝ ይደረጋል። ከዛም የትእይንቱ ጅማሬ ይሆናል። 

ጨዋታው የሚጀመረው በቁየ ወይም በሩር ጨዋታ ትልቅ ተሰጥኦ ያላቸው ሁለት ሰዎች ሩሩን ወደ ሰማይ በመወርወር አየር ላይ የቀደመው በመቅለብ ከወደቀም በፍጥነት በመጠለዝ ነው።

ጨዋታው እንደ ቡድን ጎል በማግባት ሳይሆን ሁሉም ወደ ራሱ ሰፈር ሰፊ መንገዶች ወይም ጀፎሮዎችን ተከትሎ ሩሯን በመምታት ወደ ራሱ መንደር ለማድረስ በመጫወት ነው የሚካሄደው፡፡

የተጫዋቾችም ቁጥርና ሰአት ገደብ የለውም፡፡ ሁለቱም በጋራ ወስነው በሁለቱም አቅጣጫ እዚህ መንደር ያደረሰ አሸናፊ ይሆናል ብለው ይስማማሉ። በመሆኑም ሩሩን እየመቱ ይነጉዳሉ። ጨዋታውን ወደ አሰቡት ሩቅ ሰፈር ያስጓዘ የተወሰነው ቦታ ሲደርስ ቡድኑ እንዳሸነፈ ይቆጠርለታል፡፡ ይህ አሸናፊ ቡድን ዓመቱን ሙሉ እንደተከበረ እንደ ተወራለት ይከርማል።

ለቀጣይ ዓመትም በአካባቢው ልጅ ያላገኙ የትዳር አጋሮች ያሉበት እንዲሁም በተከታታይ ሴት የወለዱ ወንድ ልጅ ለመውለድ እንዲሁም በተቃራኒው በተከታታይ ወንድ ልጀ የወለዱ ሴት ለመውለድ የሚመኙ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ ለዓመቱ ስለት እንዲሳሉ ለማድረግ የመጫወቻ ዱላዎቹን ደጃፎች ላይ የመጣል ባህላዊ ስርዓትም ይከናወናል።

ወጣቶቹም በመመካከር በትሮቹን ከአንዷ ደጅ ይጥላሉ። ለከርሞም ባለተራዋም ጓጉታ ትጠብቃለች። “እኔ ደጅ ጣሉልኝ” ብላ አፍ አውጥታ የምትጠይቅም ትኖራለች። ልጆቹም በራፍ ላይ የገና መጫወቻ ድቤ ይዘው በግጥምና ዜማ  ተሰብስበው ይጫወታሉ።

ለበሞ እያሉ አዚመው ለዓመቱ በሰላም እንዲያደርስ ፈጣሪን ተማፅነው ልጅ ይወለድ ዘንድም ተመኝተው መጫወቻቸው እዚያው አስቀምጠው ነው የሚለያዩት። በሶዶ ክስታኔ የጉራጌ ማህበረሰብ ደግሞ ''ይምር ይምር'' በመባልም ይታወቃል። 


 

ከሁነቶቹ መካከል ኢምር ኢምር አንዱና ዋነኛው ሲሆን በአካባቢው አብሮ አደግ ሴት ልጃገረዶች በመጠራራት ከየቤታቸው በእናታቸው የተዘጋጀላቸውን ጠላ በጣሳ፣ ቆሎውን በሌማት እንዲሁም ወንፊት(ጎንቺት)ና ከበሮ በመያዝ ተሰባስበው ወደ ፀሐይ መውጫ ፊታቸውን በማዞር ይቀመጣሉ። ከቻሉ በቁጥራቸው ልክ ወንፊት ይይዛሉ። 

ካልቻሉም በእድሜ ታላቋ ትይዛለች። ቀጣዩ ተግባር ፀሐይዋን በወንፊቱ ቀዳዳ እያዩ ''ኢምር ኢምር'' እያሉ እስከ አስራ ሁለት ጊዜ በመቁጠር ምስጋናቸውን የማቅረብ ስርዓት ያከውናሉ።


 

ልጃገረዶቹ ይህንን ካደረጉ በኋላ ቆሎው፣ ጠላውና ዳቦውን ከወንፊቱ ስር አድርገው፦

    ''ኢምር ኢምር ቦግ ቤል...ኢምር ቦግ ቤል

     ዬዳኮኛ ኧቡር ተክ ቤል''...እያሉ ይጫወታሉ። 

''ፀሐይ ሆይ ፈካ በይ

የእናታችን ጠላት ዱብ በይ'' እንደማለት ነው። 

ከዚያም ሴት ልጃገረዶቹ ከየቤታቸው ይዘውት የመጡት ጠላ በአንድ እንስራ እንዲሁም የያዙት የገና ቆሎአቸውን አንድ ላይ በማድረግ በአንድነት በህብረት በፍቅር እየበሉ እየጠጡ ከበሮ በማንሳት ባህላዊ ጭፈራቸውን ይጨፍራሉ፤ ይደሰታሉ ፤ይዝናናሉ።

ከኢምር ኢምር ሁነቱ በዘለለ በወጣት ወንዶች ጎራ ደግሞ በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው የገና ዱላቸውን በመቁረጥ ያዘጋጃሉ "አንቃት" ሩር ያስተካክላሉ። በዓሉም ከመድረሱ ቀደም ባሉት ቀናቶች በየአካባቢያቸው የገና ጨዋታ ይጫወታሉ።

በመጨረሻው የገና ዕለትም የገና ጨዋታ ሲጫወቱ የዋሉ ወንዶችም ባህላዊ ዘፈን እየጨፈሩ ወደ መንደር በመምጣት የተዘጋጀላቸውን ዳቦ ይበላሉ፤ይጨፍራሉ፤ ይደሰታሉ፡፡


 

ኢምር ኢምር ጨዋታ በአካባቢው ለባል የተሰጠች ልጃገረድ ጓደኞቿን (የጎስቴ) ቤት ድረስ በመጥራት የአካባቢው ኮረዳዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ከየቤታቸው ጠላና ቆሎ ይዘው በመሄድ አንድ ላይ ተቀምጠው ፊታቸውን ወደ ፀሐይ መውጫ በመመለስ በወንፊት መሀል አይናቸውን አድርገው ወደ ሰማይ በመመልከት የሚጫወቱት ጨዋታ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም