በገና በዓል በእርድ እንስሳትና በግብርና ምርት አቅምን ያማከለ አቅርቦት አለ-ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
በገና በዓል በእርድ እንስሳትና በግብርና ምርት አቅምን ያማከለ አቅርቦት አለ-ሸማቾች
ደብረ ብርሃን/ወልድያ፤ ታህሳስ 28/ 2018 (ኢዜአ)፡- በገና በዓል የእርድ እንስሳትና የግብርና ምርቶች አቅርቦት አቅምን ያማከለ መሆኑን የደብረ ብርሃንና ወልድያ ከተሞች ሸማቾች ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሮቹ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎች በበኩላቸው በቅድመ ዝግጅት ወቅት በተሰራው በርካታ ስራ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር አስችሏል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪው አቶ ደመዋዝ አጥላው ለኢዜአ እንደገለጹት ለገና በዓል የእርድ እንስሳት በዋጋም ሆነ በአቅርቦት አማራጭ በመኖሩ በአቅማቸው ለመሸመት ችለዋልⵆ
በዓሉን በለመዱት የመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅ ለማሳለፍ ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል።
ሌላዋ ሸማች ወይዘሮ ትርንጎ በየነ በበኩላቸው ለበዓል መዋያ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ቀይ ሽንኩርት በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ጠቁመዋል።
የገና በዓል የስጦታና የመጠያየቅ በመሆኑ ለበአሉ ከገዙት ላይ በማካፈል በደስታ ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የግብይት ባለሙያ አቶ ጎበዜ ማርእሸት እንዳሉት ለገና በዓል የእርድ ከብት፣ ዶሮና እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ በሸማች ማህበራት በኩል ቀርበዋል።
በተያያዘ ዜና በወልድያ ከተማ ለገና በዓል የእርድ እንስሳትና የግብርና ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸውን ሸማቾች ገልጸዋል።
በከተማዋ በግ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ መዝገቡ አስፋው ለኢዜአ እንዳሉት የበዓል ገበያ አቅርቦቱ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።
እርሳቸውም የአቅማቸውን በመግዛት ከቤተሰብና ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በፍቅር ለማሳላፍ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ ዘነቡ ተፈራ በበኩላቸው ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን በአቅማቸው መግዛታቸውንና በዓሉን በደስታ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከከተማው መደበኛ ገበያዎች በተጨማሪ በጊዜያዊነት ያቋቋማቸው የመገበያያ ቦታዎች ግብይቱ እንዲሳለጥ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።