በአዳማ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ምርቶች እና ሸቀጦች በስፋት ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ምርቶች እና ሸቀጦች በስፋት ቀርበዋል
አዳማ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአዳማ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የእርድ እንስሳትን ጨምሮ ምርቶች እና ሸቀጦች በስፋት መቅረባቸውን ነጋዴዎች እና ሸማቾች ገለፁ።
ኢዜአ ካነጋገራቸው ሸማቾች መካከል አቶ ነጋሽ ሃይሌ በሰጡት አስተያየት፤ ለገና በዓል ከጎረቤቶቻቸው ጋር ለቅርጫ የሚሆን በሬ ለመግዛት መምጣታቸውን ገልጸው ለበዓሉ የሰንጋና የድልብ በሬዎች በቂ አቅርቦት እንዳለ ተናግረዋል።
አቅርቦቱ በበቂ መጠን ቢኖርም የበሬ ዋጋ ከአምና ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ለምለም ቃሲም በበኩላቸው፤ የእርድ እንስሳት ገበያው ካለፈው የገና በዓል ጋር ሲነፃፀር በአቅርቦት በኩል የአሁኑ የተሻለ ነው ብለዋል።
የሀበሻ ዶሮ በአንድ ሺህ 500 ብር መግዛታቸውን ጠቅሰው በከተማዋ ለበዓል የሚያስፈልጉ ሸቀጣ ሸቀጦችን ጨምሮ የእርድ እንስሳት አቅርቦት ችግር እንደሌለ መታዘባቸውን ተናግረዋል።
ሰንጋ በሬዎችን ለገበያ ያቀረቡት ሳሀሊ ሀጂ ከድር፣ ከ80 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር በሆነ ዋጋ እየሸጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ለገና በዓል በዛር እና ኤግዚቢሽን ያዘጋጀው የአዳማ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ግርማ፣ በባዛሩ ላይ የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች በስፋት መቅረባቸውን ገልጸዋል።
በባዛሩ ላይ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች፣ ፋብሪካዎች፣ አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ ነጋዴዎች፣ የሕብረት ስራ ማህበራትና የተለያዩ አንቀሳቃሾች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት መቅረባቸውን አመላክተዋል።
ሕብረተሰቡም ከእንቁላል ጀምሮ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ መሆኑንም አስታውቀዋል።