የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2018(ኢዜአ)፦የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር ከጸሎትና ምስጋና ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አባቶች ነገ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም፥ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በምስጋና ብቻ ሳይሆን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፤በዓሉ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር የገለጸበት ነው ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮችም የልደት በዓልን ሲያከብሩ ለፈጣሪ ጸሎትና ምስጋና ከማቅረብ ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚህም በተለያየ ምክንያት የምግብ፣የልብስና መጠለያ እጥረት የገጠማቸውን ወገኖች በማገዝ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መደገፍና ማገዝ እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው፤ የኢየሱሰ ክርስቶስ ልደት ሲከበር አቅመ ደካማና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም በዓሉ ሲከበር ሕሙማንን በመጠየቅ፣አቅመ ደካማና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች ካለን በማካፈልና የታረዙትን በማልበስ ማሳለፍ ይገባናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ፥ በኢትዮጵያና በተለያዩ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የደስታና የፍቅር እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነትና ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ልዩነቶችን በእርቅ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እንትጋ ብለዋል ቄስ ደረጄ ጀምበሩ፡፡