የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 51ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 51ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 51ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም መሰረት፦
1. በቅድሚያ ምክር ቤቱ የተወያየው የማዳበሪያ ምርት ፈቃድ እና የፖታሽ ማዕድን ምርት ፈቃድ ረቂቅ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ለምክር ቤቱ የቀረቡት ሁለት ረቂቅ ስምምነቶች የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ ሀገራችን ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት እና ለሀገራችን አርሶ አደሮች ወቅቱን የጠበቀ የማዳበሪያ ስርጭት እንዲኖር ለማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸውና ከአካባቢ ጥበቃና ከማህበረሰብ ተጠቃሚነት አንጻርም የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ የማዕድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረምና ወደ ስራ እንዲገቡ ምክርቤቱ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡
2. በመቀጠል የቤት ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ምከር ቤቱ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ ባለፉት አመታት በቂ የቤት አቅርቦት እንዲኖር የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም አሁንም የቤት አቅርቦትና ፍላጎት የተጣጣመ አይደለም፡፡ በመሆኑም በከተማና በገጠርለሚኖሩ ለሁሉም ዜጎች አቅምን ያገናዘበ፣ ተደራሽ እና በቂ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በምክር ቤቱ ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር በተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ላይ ነው፡፡ የብድር ስምምነቱ ለህከምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጄክት ምዕራፍ 2 ማስፈፀሚያ የሚውል 30,000,000 /ሰላሳ ሚሊዮን/የአሜሪካን ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን የሀከምና መሳሪያዎችን ችግር የሚፈታ፣ ዝቅተኛ ወለድ 0.01% የሚከፈልበት እና የከ5 አመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምከር ቤቱም ብድሩ ከሀገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋርየሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ለሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ከፍያን ለመወሰን የወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ ለተገልጋዮች ጥራትና ተዓማኒነት ያላቸው አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያወጣቸውን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ወጪዎች የአገልግሎቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከሆነው የህብረተሰብ ክፍል ተመጣጣኝ ከፍያ በማስከፈል እንዲሸፍን ለማድረግ እንዲያስችለው ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምከር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይበሰፊው ከተወያየበት በኋላ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ደምጽ ወስኗል፡፡
5. እንዲሁም የኅብረት ሥራ ማህበራት ማሻሻያ አዋጅ ምክር ቤቱ የተወያየበት ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ በስራ ላይ ያለው የኅብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ ቁጥር 985/2009 ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከተቀመጡ አቅጣጫዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
6. በማስከተልም የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቷል፡፡በአየር ትራንስፖርት ደህንነት፡ አስተማማኝነትና ቅልጥፍና ላይ የሚስተዋሉ የደህንነት ስጋቶችን በብቃት ለመከላከል የሚያስችል አሰራር ለመተግበርየአቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅ ቁጥር 432/1997ን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማሻሻያ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
7. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በሁለት ደንቦች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው የመሶብ አገልግሎትን ለማቋቋም የወጣው ደንብ ተገልጋዮች የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት የሚያባከኑትን ጊዜ፣ ወጭ እና ጉልበት በመቆጠብ የተገልጋይ እርካታን የሚጨምርየአንድ ማእከል አገልግሎት አሰጣጥ ለመተግበር እንዲያስችል የቀረበ ሲሆን ሁለተኛው የኢትዮጵያ የብቃትና ሥራ አመራርኢንስቲትዩት አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የወጣው ደንብ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡ምክር ቤቱም በሁለቱም ደንቦች ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረጉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
8. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የሁሉን አቀፍ የተደራሽነት ፈንድ የገቢ መጠን፣ ምንጭ እና አስተዳደርን ለመወሰን የወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ ደንቡ በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 148/2011 አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ (3) መሰረት የተቋቋመው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት ፈንድ የገቢ መጠንና ምንጭ እንዲሁም ፈንዱ ስለሚተዳደርበት ሁኔታ ለመወሰን ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው፡፡ ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
9. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ የስፖርት ፖሊሲ ላይ ነው፡፡ በስራ ላይ ያለው የስፖርት ፖሊሲ የማህበረሰቡን የስፖርት ተሳትፎ ከማረጋገጥ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርአት ከመዘርጋት፣ ንጹህ ስፖርትን ለማስፋፋት የአበረታች ቅመሞችና ዘዴዎች ከመከላከል እና ስፖርትን ለማህበራዊ ልማት ከመጠቀም አንጻር ከፍተቶች የነበሩበት በመሆኑ ፖሊሲውን ለማሻሻል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
10. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የፌዴራል ስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ የስፖርት ዘርፍ ካለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዲሁም አስተዳደራዊ ውስብስብነት አንጻር ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት ዘመናዊ፣ አሳታፊና አካታች የሆነ የህግ ማዕቀፍና አስተዳደራዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡