ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለገና በዓል ለአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ማዕድ አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለገና በዓል ለአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ማዕድ አጋራ
ጂንካ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ100 አቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ማዕድ አጋራ።
የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ካሳሁን የማነ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በማህበረሰብ አገልግሎት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በተለያዩ ጊዜያት ሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ ለማህበረሰቡ ያለውን አለኝታነት በተግባር ሲያሳይ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በዛሬው እለትም የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ለ100 አረጋውያንና አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ በማድረግ ማዕድ ማጋራቱን ገልጸዋል።
በድጋፉም ለእያንዳንዳቸው የዳቦ ዱቄትና የዘይት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ ተቋሙ የበጎ አገልግሎት ተግባሩን በቀጣይም ያጠናክራል ብለዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው አቅመ ደካማ ወገኖች መካከል ወይዘሮ አለሚቱ በቀለ፤ ዩኒቨርሲቲው በዓል በመጣ ቁጥር የበዓል መዋያ ድጋፍ በማድረግ ተደስተው እንዲያሳልፉ እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዓልን ያለሀሳብ እንዲያሳልፉ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፣ እንዲህ ያሉ እርስ በርስ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ልምዶች በተለይ እንደእሳቸው ላሉ አቅመ ደካሞች እፎይታን ስለሚሰጡ መጠናከር አለባቸው ብለዋል።
ሌላው ድጋፍ የተደረገላቸው አቶ አለሙ ጨነቀ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በዓል በደረሰ ቁጥር አቅመ ደካሞችን በማሰብ ለወገኑ እያሳየ ያለው አለኝታነት ለሌሎች አርአያ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በበጎ ምግባር የሚከናወኑ ሥራዎች የብዙዎችን ጭንቀት ስለሚያስቀር እንዲህ ያሉ መልካም ተግባራት በሌሎች ተቋማትም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።