ቀጥታ፡

አስተዳደሩ የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት የሚቀይሩ የልማትና የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት የሚቀይሩ የልማትና የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች 381 ቤቶችን ከሙሉ የቤት ዕቃና ከበዓል ማሳለፊያ ጋር በስጦታ አስረክበዋል።


 

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፤ የገና በዓል የፍቅር፣ የደስታና የመረዳዳት መገለጫ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ዜጎችን የቤት ባለቤት በማድረግ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ መርሃ ግብሩን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።  

በዚህም መሠረት በዛሬው ዕለት በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተገነቡ 381 ቤቶች ቁልፍ ለአቅመ ደካሞችና ለሀገር ባለውለታዎች መተላለፉን አስታውቀዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰው ተኮር ሥራዎችን በማከናወን ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በቀጣይም የዜጎችን ሕይወት በዘላቂነት የመቀየር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

ቤት ከተሰጣቸው መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት ደራሲ ሀብታሙ አለባቸው፤ ለረጅም ጊዜ በቤት ችግር ውስጥ ለኖረ ሰው እንዲህ ዓይነት ድጋፍ ማግኘት ልዩ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸው፤ ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።


 

አቶ ኤልያስ አብዲሳ አጋ በበኩላቸው፤ ለሀገር ባለውለታ የሆኑትን አባታቸውን በማሰብ የከተማ አስተዳደሩ ላደረገላቸው የቤት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ አጋጣሚ ለእሳቸውና ለቤተሰባቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለውም አክለዋል።


 

ቀደም ሲል የነበረብኝ የመጠለያ ችግር በአስተዳደሩ ተቀርፎ ደስ ብሎኝ በሰላም የምኖርበትን ቤት በማግኘቴ አስተዳደሩን አመሰግናለሁ ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አያልነሽ ብርሃኑ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም