ቀጥታ፡

ለገና በዓል የእርድ እንስሳት እና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት ችለናል-ሸማቾች

ወልቂጤ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን ለገና በዓል የእርድ እንስሳትና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸመቱ መሆናቸውን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በዞኑ በአበሽጌ ወረዳ ዋልጋ ገበያ የእርድ ከብት ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ያለው በለጠ፤ ገበያው ላይ የእርድ ከብቶች በግ፣ ፍየል እና በሬ በበቂ መጠን መቅረቡን ተናግረዋል ።

በዚህም እንደየአቅምና ፍላጎት አማርጦ ለመግዛት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠሩን ነው የገለጹት።


 

እሳቸውም በአቅማቸው ልክ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ለአራት የቅርጫ በሬ መግዛታቸውን ጠቅሰው በዓሉን ከአቅመ ደካሞች ጋር ማዕድ በመጋራት ለማክበር ተዘጋጅተናል ነው ያሉት። 

የበሬ ነጋዴ የሆኑት አቶ ጅላሉ ወርቁ፤ በበዓል ገበያው ሸማቹ እንደየአቅሙ ለመሸመት የሚያስችል የእርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ መቅረቡንና ዋጋውም ተመጣጣኝ መሆኑን አንስተዋል ።

አቶ ጅላሉ አክለውም ለግብይት የሚሆን ገንዘብ በኪስ ይዞ ከመንቀሳቀስ ዲጂታል አማራጭ እንደሚጠቀሙ ጠቅሰው ይህም ከስርቆትና መሰል ስጋቶች ይታደጋል ብለዋል ።

አሁን ላይ የዲጂታል ግብይት አማራጭ እየተለመደ መምጣቱ ስራው ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻሉን ጠቅሰው በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚታየው የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት መሰራት አለበት ብለዋል።

ሌላኛዋ በዞኑ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሰለች ዘበርጋ ለበዓሉ ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ዶሮ፣ እንቁላል እና ሽንኩርት  በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ያስችላል ብለዋል።


 

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለበዓሉ የሚሆኑ የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀደም ብለው መቅረባቸው ገበያውን የተረጋጋ አድርጎታል ያሉት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት እፀገነት ተበቃ ናት።

የከተማ አስተዳደሩ ዋጋን ከመቆጣጠርና የምርት አቅርቦት ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ የሰጠው ትኩረት ገበያው እንዲረጋጋ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉንም አቅመ ደካማ ወገኖችን በመጠየቅ እንሚያሳልፉትም ጠቁመዋል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበው ግብይት እየተከናወነ መሆኑን የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ውድማ አረጋግጠዋል ።


 

በተለይም ምርቶቹ ከደላላና መሰል ጣልቃ ገብነት በጸዳ መልኩ በቀጥታ ለሸማቹ እንዲቀርብ ከአምራቾች ጋር ትስስር መፈጠሩ ገበያውን ማረጋጋቱን ጠቅሰው ሸማቹ የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማስቻሉን አብራርተዋል።

ምርት የሚደብቁ፣ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉና ባዕድ ነገሮችን የሚቀላቅሉ አካላትን አሳታፊ በሆነ መልኩ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ታምራት በሁሉም አካባቢዎች የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም