በገናና የጥምቀት በዓላት ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎች አዳዲስ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚጎበኙበት ዕድል ተመቻችቷል - ኢዜአ አማርኛ
በገናና የጥምቀት በዓላት ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎች አዳዲስ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚጎበኙበት ዕድል ተመቻችቷል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦በገናና የጥምቀት በዓላት ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎች አዳዲስ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚጎበኙበት ዕድል መመቻቸቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ኃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት መካከል ገናና ጥምቀት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በዓላቱ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ኃይማኖታዊ እሴት ለውጭ ጎብኚዎች በአግባቡ ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
በተለይም ገና እና ጥምቀት ላሊበላና ጎንደርን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ የሚከበር ሲሆን በዓሉን ለመታደም የሚመጡ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ የተገነቡ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አሁን ላይ ከውጭ ሀገር ባለፈ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የገናና የጥምቀት በዓላት ከእምነቱ ተከታዮች ባሻገር የውጭ ጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ታላላቅ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ናቸው።
በበዓላቱ ለመታደም የሚመጡ ጎብኚዎች የኢትዮጵያን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችንና የአደባባይ በዓላትን በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ ዕድሎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በበዓላቱ ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎች የተሻለ የቆይታ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚያስችል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የገናና የጥምቀት በዓላት በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎችም ለባለድርሻ አካላት ሥልጠና በመስጠት የቱሪስቶችን የአገልግሎት እርካታ ለማሳደግ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ከዓለም ክፍሎች በገናና የጥምቀት በዓላት ለመታደም ለሚመጡ ጎብኝዎችም በተለያዩ የመረጃ አማራጮች የበዓላቱን ታሪካዊ ዳራና በድምቀት የሚከበርባቸወን ሥፍራዎች የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር አስተባባሪነት አስጎብኝዎችና ባለድርሻ አካላት አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ ጭምር የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የተሻለ የሚያድርግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በተቀረጹ የጉብኝት ፓኬጆችም የገናና የጥምቀት በዓላትን ለመታደም የሚመጡ ጎብኝዎች አዳዲስ የመስህብ ሥፍራዎችን የሚጎበኙበት ዕድል መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የተሻለ የጉብኝት ምኅዳር ለመፍጠርም አስጎብኝዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።