ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት መሰረት እየጣለች ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የፖሊሲ ማዕቀፍ እና መሰረተ ልማትን ጨምሮ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጽሑፍ አቅርበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ.አይ) በዓለም ደረጃ ያለው ተጽእኖ እና ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው የ2025 የፈረንጆቹ ዓመት ኤ.አይ በርካታ ስራዎችን መተካቱን አውስተው አሁንም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ፈጥነን ልጆቻችንን ካዘጋጀን ሰው ሰራሽ አስተውሎትን እንደ ተለያዩ ምርቶች በቀላሉ መጠቀም እንችላለን ብለዋል።

ኤ.አይ ስራ ይቀማል ብዬ አልሰጋም ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሰው ልጅ መስራት የሰው ልጅ ሊሰራቸው የማይገባቸውን ስራዎች እየተካ ይሄዳል ነው ያሉት።

ኤ.አይን የምንፈጥር እኛነን ኤ.አይን የምንቀይር እኛ ነን ቀድመን ግን ፋውንዴሽን መጣል ይገባናል ብለዋል።

መንግስት ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው ሳይንስ ሙዚየም አንዱ መሰረተ ልማት መሆኑን ተናግረዋል።

መሰረተ ልማት እና ታለንት ለዘርፉ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱም ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የምትገነባው የኤ.አይ ዩኒቨርሲቲም የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን ብዙ ችግሮች ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን ተናግረዋል።

ዋናው ለልጆቻችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጆቻችን የሚወዳደሩበት ልጆቻችን ከሌላው አንስው የማይታዩበት ሁኔታ ለመፍጠርም እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ቀድሞ መወዳደር ቀድሞ መገኘት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ኤ.አይን በዛ መልክ ማየት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኤ.አይ ስራዎችን በማቃለል እና ጊዜ በመቆጠብ ወሳኝ ድርሻ እንደሚወጡም ነው የገለጹት።


 

ተማሪዎችም ኤ.አይን መጠቀም አለባቸው፤ ቴክኖሎጂዎቹን መጠየቅ እንዲችሉ አድርገን ከፈጠርናቸው ተማሪዎች ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የመጠየቅ ብቃት ችሎታ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድም ኤ.አይ የተማሪዎችን አቅም እንደሚገነባ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ትውልድ ለኢኮኖሚ ቅድሚያ የሰጠ እና ሁለተኛው ትውልድ ፖለቲካዊውን ያስቀደመ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሁኑ ዘመን የሀሳብ ትውልድ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሀሳብ የሚወድ ትውልድ ችግሮች እየፈታ እና እያቀለለ እንደሚሄድም ተናግረዋል።

ኤ.አይ ዝግጅት እና ስራ እንደሚፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመፍራት ይልቅ እውነታውን በመጋፈጥ ማሸነፍ እንችላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም