ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር፣ የዲሞክራሲ ባህልና የተቋማት ግንባታ ለሁሉም የምትመች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 28/2018(ኢዜአ)፡- ሀገራዊ ምክክር፣ የዲሞክራሲ ባህልና የተቋማት ግንባታ ሥራዎች ለሁሉም የምትመች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሰረት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያን ችግሮች በመፍታት በተደመረ አቅም ሀገርን ለማበልፀግ ምሁራን ሀሳብ ከማመንጨትና ችግር ፈች ጥናት ከማድረግ ጀምሮ በተግባር ለውጥ የሚያመጣ ሥራን ሊከውኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት “የምሁራን ሚና ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችን መፍታት የቁርጠኝነትና የአቋም ጉዳይ መሆን አለበት ብለዋል።

በየአካባቢው ያሉ የጽንፍ እሳቤዎች ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንደማይወስዱ በማንሳት፥ ኢትዮጵያ የጋራችን ናት በሚል እሳቤ አምነን ከሠራን ወደተሻለ ምዕራፍ እንሻገራለን ነው ያሉት።

ታሪክን በሚዛን፣ ዛሬን በትጋት፣ ነገን በተስፋ ነው የምንመለከተው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለሁሉም ህብረተሰብ እኩል እድል መስጠት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ጠንካራ ሀገራዊ አንድነት መፍጠር የሚቻለው የወል ትርክት በመገንባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም