ከተማርንና ዝግጁ ከሆንን በኤ አይ የማይናቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከተማርንና ዝግጁ ከሆንን በኤ አይ የማይናቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 28/2018(ኢዜአ)፡- ከተማርንና ዝግጁ ከሆንን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሂደት የማይናቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጽሑፍ አቅርበዋል።
ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላም ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅትም፤መንግሥት የኮሪደር ልማትና መንገድ ሠርቶ ለነዋሪው ሲያቀርብ ይህን በአግባቡ እንዴት መያዝ እንደሚቻል ደግሞ ምሁራን ከተሜነትን የሰው ልጅ ዐዕምሮ ላይ መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ኤ አይ ከሚፈልጋቸው ነገሮች አንዱ ኢነርጂ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ብዙ የማምረት ዐቅም እንዳላት አረጋግጠዋል።
ኢነርጂ ላይ ኢንቨስት ካደረግን ለኤ አይ አንድ አስቻይ ጉዳይ ፈታን ማለት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ሌላው ኤ አይ የሚፈልገው ጉዳይ መረጃ(ዳታ) እና የመረጃ ማዕከል(ዳታ ሴንተር) መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከተማርን፣ ዝግጁ ከሆንን፣ እየሠራናቸው ያሉትንና በቀጣይ የምናከናውናቸውን ጨምሮ በመተባበር ለለውጥ ዝግጁ ሆነን በትጋት ከሠራን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሂደት የማይናቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብለዋል።
ለኤ አይ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮች በብዛት በአፍሪካ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል።