ቀጥታ፡

የነበርንበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለናል - የቀድሞ ታጣቂዎች

ጎንደር፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ የነበርንበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለናል ሲሉ በአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ።

በክልሉ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን ጥሪ በመቀበል የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ለመንግስት በማስረከብ በጠዳ የስልጠና ማእከል የተሀድሶ ስልጠና ጀምረዋል።


 

በስልጠና ላይ ካሉት የቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው አስቻለው እሸቴ፣ አስቻለው ዳርጌ እና አንዳርጌ ሲሳይ፤ የነበርንበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በአግባቡ በመረዳት የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ብለዋል።

በክልሉ የውክልና ጦርነት ተልእኮ ፈፃሚ በመሆን ሰላምን ማናጋትና ህዝብን መጉዳት ታጋይነት ሳይሆን ባንዳነት መሆኑን ያነሱት ሰልጣኞቹ የነበርንበት መንገድ ፍፁም ስህተት መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉ ተናግረዋል።


 

ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አስቻለው እሸቴ፤ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ ወጥተን መጥተናል፤ የበደልነውን ህዝብም በልማት ለመካስ ተዘጋጅተናል ብሏል።

በክልሉ የተሳሳተ መንገድ ላይ የነበሩ ወጣቶች እየተመለሱ መሆኑን አንስቶ እርሱና ጓደኞቹም ይህንኑ እድል በመጠቀም መምጣታቸውን ተናግሯል።

በመሆኑም ሌሎችም ጊዜ ሳያባክኑ ትጥቃቸውን በማስረከብ ለሰላማዊ ህይወት ተዘጋጅተው እንዲመጡ መልእክቱን አስተላልፏል።

ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ አስቻለው ዳርጌ፤ የመንግስትን የሠላም ጥሪ በመቀበል ሰርቶ ለመለወጥና የሰላም አምባሳደር በመሆን ህዝብን ለማገልገል መምጣቱን ተናግሯል።


 

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የጥፋት መሳሪያ መሆን ከባንዳነት ውጭ ሌላ ትርጉም የሌለው መሆኑን አንስቶ፤ በጥፋቱ በመፀፀት ህዝብን በልማት ለመካስ መምጣቱን ገልጿል።


 

በመሆኑም የመንግስትን የሠላም ጥሪ በመቀበል ስልጠናውን ወስዶ ወደ ነበረበት ሰላማዊ ህይወት በመመለስ የበደለውን ህዝብ በልማት ለመካስ መዘጋጀቱን ገልጿል።

የአማራ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ በሪሁን መንግስቴ፤ የመንግስትን የሠላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በየእለቱ እየመጡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የቀድሞ ታጣቂዎቹን በመቀበልና የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት መልሰው እንዲቋቋሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በክልሉ እየመጣ ላለው ሰላም የመንግስት ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ በተለይም የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አጠቃላይ የህዝቡ ድምር ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም