ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው የጋራ ዕድገትና ደህንነት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ሀገራት የጋራ ዕድገትና ለአካባቢው ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ በተፈጸመባት ኢ-ፍትሐዊ ሴራና ሸፍጥ ካለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ወዲህ የራሷ ከሆነው የቀይ ባሕር ቀጣና እንድትገለልና የባሕር በሯን እንድታጣ ተደርጓል።

ኢትዮጵያ በተፈጸመባት የታሪክ ስብራት ባህር በር አልባ መሆኗ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷንና የህዝቧን  ፍላጎት በሚፈለገው ልክ ለማሟላት ተግዳሮት መፍጠሩ ይነሳል።

አሁን በይፋ ያነሳችው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያለው ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለሠ መና፤ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት መንገድ ሕዝብን ያላሳተፈና ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጥያቄ ማቅረቧ ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚመነጭ መሆኑንም ገልጸዋል።

የባሕር በር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጥያቄውም የዓለም አቀፍ የሕግ ሥርዓትን የተከተለና ምክንያታዊ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህልውና ከቀይ ባሕርና ዓባይ ወንዝ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው ያሉት አቶ መለሠ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም ቀጣናዊ የጋራ ዕድገትን የሚያሳልጥና በብዙ መመዘኛም አሳማኝ ነው ብለዋል።

የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት የጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረትም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም የሀገርን ስትራቴጂካዊ ጥቅምና ክብር የማስጠበቅ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ የሀገርን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ፍላጎት ከግምት ያስገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ጎረቤት ሀገራትን በሁሉም መስክ  የጋራ ተጠቃሚ የሚያድርግ የአካባቢውን ደህንነትም  ለማስጠበቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የቀረበውን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ለማስገኘት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም