ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የቱሪስት መስህቦችን በማልማት የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር ትኩረት ተሰጥቷል

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የቱሪስት መስህቦችን በማልማትና አሰራርን በማዘመን የጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመርና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ የተቀናጀ የቱሪዝም አስተዳደር ሥርዓት ሥራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ ላይ የቢሮው ሃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ፤ የክልሉን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ የመስህብ ሀብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፍን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ  የ25 ዓመት አሻጋሪ የእድገትና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ተነድፎ እየተተገበረ መሆኑንም ገልፀዋል።

ለዚህም በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት ሃብቶችን በጥናት በመለየት በዘላቂነት የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል። 

በተለይ ለቱሪስቶች የላቀ አገልግሎት በማቅረብ ቁጥራቸውን የማሳደግና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም የሚያስችሉ ተግባራት በቅንጅት እየተሰሩ ነው ብለዋል።


 

የተቀናጀ የቱሪዝም አስተዳደር ስርዓት ሥራ መጀመርም የቱሪዝም ፀጋዎችን፣ መዳረሻዎችን፣ ምርትና አገልግሎቶች የተመለከቱ መረጃዎችን  በቴክኖሎጂ  በማደራጀት  ከአንድ ማዕከል ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።  

ይህም በተበታተነ መንገድ ለቱሪስቱ ይደርስ የነበረውን መረጃ በቅንጅትና በፍጥነት በማቅረብ የአገልግሎት ልህቀትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ነው ያስታወቁት።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው በበኩላቸው፣ በክልሉ አሰራሮችን ዘመኑን በሚመጥን አግባብ በቴክኖሎጂ ለማገዝ እየተሰራ ነው።


 

የተቀናጀ የቱሪዝም አስተዳደር ስርዓትም የቱሪዝም ዘርፋ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል አሰራር መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ሁሉንም የቱሪዝም ተዋናዮችን በአንድ ማዕከል በማምጣት የዘርፋን ንግድ ትርፋማነት የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለጎብኚዎች ፍላጎትና ጊዜን መሰረት ያደረገ ትክክለኛ አገልግሎት ከማቅረብ ባለፈ ዘርፋ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን የጎላ ሚና ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልል አመራሮች፣ የዘርፉ ተዋናዮች፣ የቢሮው ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም