ቀጥታ፡

በካፋ ዞን የቡና ምርታማነትን ለመጨመር የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 27/2018(ኢዜአ)፡-በካፋ ዞን የቡና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

ዞኑን የቡና ልማትና ግብይት ማዕከል በማድረግ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ መምሪያ አስታውቋል።

ካፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና አረቢካ መገኛ ተደርጋ የምትጠቀስ ሲሆን ይህ ዞን በዩኔስኮ በባዮስፌር ሪዘርቭ የተመዘገቡ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን ያለበትም አከባቢ ነው፡፡

አሁንም ድረስ የጫካ ቡና በስፋት የሚገኝበትና የተፈጥሮ ደኑ ሚዛን ተጠብቆ የቆየበት አከባቢም ነው፡፡

የቡና ቱሪዝምን በማነቃቃት ጎብኚዎችን ለመሳብ በመገናኛ ብዙኅን ሙያተኞች አማካኝነት በዋና ዋና የቡና አብቃይ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ መደረጉ ይታወቃል።


 

በዚሁ ወቅት የካፋ ዞን ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ሥራ መምሪያ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሞገስ ተክሌ እንዳሉት፤ ዞኑ ቡናን ጨምሮ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድጉ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለ ነው።

የዞኑ የመሬት ሽፋን 53 በመቶ ያህሉ በደን የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመው፤ በውስጡም ቡና፣ ቅመማ ቅመም፣ የተለያዩ ዕፅዋቶች፣ ብርቅዬ አእዋፋትና ንብ ይገኙበታል ብለዋል።

የካፋ ማኅበረሰብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከቡና ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ የተፈጥሮ ሀብቱን ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቆይ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በአነስተኛ መጠን ይከናወን የነበረው የቡና ልማት ሥራ አሁን ላይ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲሸፍን መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም የቡና የልማት ሥራው በየዓመቱ በአስር ሺህ ሄክታር መሬት እንዲጨምር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡


 

ቀደም ሲል አነስተኛ የነበሩ የቡና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር አሁን ላይ ወደ ከሁለት መቶ በላይ ከፍ እንዲል መደረጉን ጠቁመው፥ ከሶስት መቶ በላይ ቡና አቅራቢ ነጋዴዎች በዘርፉ እየተሳተፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የቡናን ምርታማነት ለማሳደግ በተከናወኑ የቴክኖሎጂና የአሠራር ለውጦች ካሁን ቀደም ከአንድ ሄክታር መሬት በአማካኝ ይገኝ የነበረው አራት ኩንታል ምርት አሁን ላይ ከስምንት ነጥብ አምስት እስከ ሀያ አምስት ኩንታል ማድረስ ተችሏል።

ይህም የዘርፉ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ተጨባጭ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ በየደረጃው የተመዘገበው ስኬት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ባለፈ ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገባት ረገድ ያለው ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም