የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ መታገዝ ሂደቱን ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ መታገዝ ሂደቱን ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒ ያደርገዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ የምርጫ ሂደት በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆን ይበልጥ ቀልጣፋ፣ ግልጽና ተዓማኒ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ30 ሺህ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ክልሎች የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል እንደሚከናወን አስታውቋል።
ቦርዱ ዲጂታል የመራጮችና የዕጩዎች ምዝገባ ሥርዓትን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን በገለልተኝነትና በታማኝነት ለማስፈጸም መቋቋሙን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ቦርዱ 7ኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ለማድረግ አሰራሩን በቴክኖሎጂ እየደገፈ ነው ብለዋል።
የምርጫ ሂደትን በቴክኖሎጂ መደገፍ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ ሂደቱን ግልጽና ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
ቴክኖሎጂ ምርጫን ለማሳለጥ ያለው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስለቴክኖሎጂው አጠቃቀም በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ቦርዱ የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባን በዲጂታል መደገፉ ከወረቀት አሰራር እየወጣ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው ቦርዱ በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ ካካተታቸው ጉዳዮች አንዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ነው ብለዋል።
በዚህም 7ኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ሁለት ሶፍትዌሮች መልማታቸውን ነው የተናገሩት።
የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ በቴክኖሎጂ መታገዙ ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ ዴሞክራሲያዊ መብትን በአግባቡ ለመጠቀምና የመረጃ አያያዝ ችግርን ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።
የቦርዱን አሰራር ቀልጣፋና ዘመናዊ ከማድረግ አኳያ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ዕጩዎችና መራጮች ባሉበት ሆነው መመዝገብ የሚችሉበት ነው ብለዋል።
ከ55 ሺህ የምርጫ ክልሎች መካከል ከ30 ሺህ በላይ በሚሆኑት የእጩዎችና የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
በዲጂታል መመዝገብ ላልቻሉ መራጮችና ዕጩዎች በወረቀት የሚመዘገቡበት አሰራር መኖሩንም ነው ሰብሳቢዋ የተናገሩት።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ታድመዋል።
ቦርዱ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።