የገዳ ስርዓት እሴቶችን ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገዳ ስርዓት እሴቶችን ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው
መተሐራ ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦የገዳ ስርዓት እሴቶችን ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የቱለማ አባ ገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊ ጎበና ሆላ ገለጹ።
ከገዳ ሚችሌ ወደ ሃልችሳ የሚሸጋገረው የጎባ ስርዓት ዛሬ በመተሐራ አርዳ ጂላ ተሬ ሌዲ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱለማ አባ ገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊ ጎበና ሆላ እንደገለጹት፤ የገዳ ስርዓት ለአገር ልማት እና እድገት ጠቃሚ የሆኑ እሴቶች ያሉት ነው።
የገዳ ስርዓት እሴቶች ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እንዲውሉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የእርስ በርስ መረዳጃ ዘዴ የሆነው ቡሳ ጎኖፋ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም በክልሉ እስከ ቀበሌ ድረስ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማደረጀት በገዳ ስርዓት መሰረት ህዝቡ ፍትህ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያየ ምክንያት ተዳክሞ የነበረው የገዳ ስርዓትና እሴቱ እየተመለሰ መሆኑን የገለጹት አባ ገዳ ጎበና፤ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤት ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ትምህርት እየተሰጠበትና ህዝቡም እየተመራበት መሆኑን አውስተዋል።
የገዳ ስርዓቱን ከማጠናከርና ከማጎልበት ባለፈ ለሀገሪቷ ገፅታ ግንባታ ለማዋልና፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲውል በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት አማካኝነትም የባሊ ወይም የስልጣን ሽግግሩ እንዳይራዘም እንዲሁም የስልጣን ሽግግሩ ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
በቀጣዩ ሰኔ 2018 ዓ.ም 70ኛው የቱለማ ኦሮሞ አባገዳ ለ71ኛው አባገዳ ስልጣኑን ለማሻገር ዝግጀት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ሌላው በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት አባገዳ ሰቡ ጎዳና እንደገለፁት፤ ትናንት እና ዛሬ የተካሄደው የጎባ ስርዓት ገዳ ምን ያህል ዴሞክራሲያዊ እንደሆነ የሚያመለክት ነው ብለዋል።
በሽግግሩ መሰረትም 'ገዳ ሚችሌ ወደ ገዳ ሃልችሳ' ሽግግር ሲደረግ የከረዩ ጎሳ ስልጣኑን ወደ ዱለቻ ጎሳ አባላት ያስተላለፈበት መሆኑን ገልጸዋል።
የቦሰት ወረዳ አባገዳዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ አባ ገዳ ቁምቢ ዋቀዮ በበኩላቸው፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት የሆነው የገዳ ስርዓት ሰላም እና ልማት የሚቀጥልበትና ሀገርና ትውልድ የሚገነባበት ስርዓት መሆኑን ተናግረዋል።
ትውልዱ የገዳ ስርዓት እሴቶችን እንዲጠበቅ፣ ስርዓቱን እንዲረዳ እና እንዲተገብር ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።