የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገልን ድጋፍ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህልን በተግባር ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገልን ድጋፍ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህልን በተግባር ያሳየ ነው
ባህርዳር፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገላቸው ድጋፍ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህልን በተግባር ያሳየ መሆኑን በባህር ዳር እና በወልዲያ ከተሞች ማእድ የተጋሩ ነዋሪዎች ገለጹ።
በአማራ ክልል የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የበዓል መዋያ ማዕድ ማጋራት ተከናውኗል።
በወልድያው መድረክ ላይ የተገኙት የከተማው ከንቲባ ዱባለ አብራሬ እንደገለጹት፣ የመረዳዳት ባህልን መሰረት አድርገው የሚከናወኑ ማህበራዊ ድጋፎች በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል።
ሁላችንም የበጎነት ተግባርን አጠናክረን በማስቀጠል የገቢ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ወገኖች በዓሉን በደስታ፣ በፍቅርና በአብሮነት እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የዛሬው ድጋፍም ከበዓል መዋያ በተጨማሪ የብርድ ልብስ፣ የአንሶላ፣ የፍራሽና ልዩ ልዩ አልባሳትን ጨምሮ መደረጉን አንስተዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከልም አቶ ሞላ አይቸው እንደገለጹት፤ በእርጅና ምክንያት በቤት በመዋል ለችግር በተጋለጡበት በዚህ ወቅት አስተዳደሩ ያደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አብታ ጌታሁን፣ የበዓል ወጪያቸውን የከተማ አስተዳደሩ በመሸፈኑ ምስጋና አቅርበዋል።
በተመሳሳይም የባህር ዳር በጎ አድራጎት ማህበር በከተማዋ ድጋፍ ለሚሹ 300 ወገኖች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋርቷል።
በከተማዋ የድጋፉ ተጠቃሚ የግሽ አባይ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እማሆይ አድና ተገኘ፣ ማህበሩ በየጊዜው ጧሪና ደጋፊ ለሌለን አቅመ ደካሞች ለበዓል መዋያ ድጋፍ እያደረገልን ይገኛል ብለዋል።
የዛሬው ድጋፍም በዓልን ሳይቸገሩ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተደስተው እንዲያሳልፉ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የባህርዳር በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ይማም እንደገለፁት፤ ማህበሩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በበዓል ወቅት ተደስተው እንዲያሳልፉ በየጊዜው የዓይነት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም በባህርዳር ከተማ በ3 ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 300 ድጋፍ የሚሹ ወገኖች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።