በከተማዋ የተጀመረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል እድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የተጀመረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል እድል ይፈጥራል
ወልዲያ ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦በወልዲያ ከተማ የተጀመረው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ህብረተሰቡን በቅርበት ለማገልገል እድል እንደሚፈጥር የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።
የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመክፈቻና የአገልግሎት አሰጣጥ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ዛሬ በወልዲያ ተካሄዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የጽህፈት ቤቱ መከፈት የከተማዋና የአካባቢው ህዝብ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ባህርዳር፣ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚያደርገውን ጉዞ ያስቀራል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ከተሞቹ ሲሄድም ለትራንስፖርት፣ ለአልጋ፣ ለምግብና ሌሎች አገልግሎቶች የሚያወጣውን ወጪ የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።
የወልዲያ ከተማ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰኢድ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መከፈቱ የወልዲያንና የአካባቢውን ህብረተሰብ በቅርበት ለማገልገል የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የፓስፖርት አሰጣጥ ስርዓቱን ጥራት፣ ተደራሽነትና እርካታን በማሳደግ በቀን እስከ 800 ለሚሆኑ ሰዎች የፓስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዛሬ የምዝገባ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ፅህፈት ቤቱ የተገልጋዩን ህብረተሰብ ደህንነት በጠበቀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ተገልጋዮች ከአጭበርባሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁም መልእክት አስተላልፈዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙሐመድ አህመድ፤ የኢሜግሬሽን ጽህፈት ቤት ወልዲያ ላይ መከፈቱ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባና ባህር ዳር ከተሞች በመጓዝ ይገጥመን የነበረን እንግልት ያስቀራል ብለዋል።
የቅርንጫፉ መከፈት የመንግስት አንዱ የለውጥ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመው ለቅርንጫፉ ስኬት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።