ቀጥታ፡

ማዕከሉ በምርምር ያወጣቸውን የሰብል ዝርያዎችን ተደራሽ ለማድረግ የመነሻ ዘር ብዜት እያካሄደ ነው

ሮቤ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦የሲናና ግብርና ምርምር መዕከል በምርምር ያገኛቸውን የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የመነሻ ዘር እያባዛ መሆኑን ገለጸ።

ማዕከሉ አርሶ አደሮችና የባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የመስክ ቀን ጉብኝት አካሂዷል።

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የምርምር ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ሚደቅሳ እንዳሉት፤ማዕከሉ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በምርምር እየደገፈ ነው።


 

በተለይ ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በስንዴ፣ ገብስና ሌሎች ስምንት የትኩረት መስኮች ላይ ተመስርቶ ምርምሮችን በማካሄድ 116 የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱን አስታውሰዋል።

ማዕከሉ በቅርብ ጊዜ በምርምር ያወጣቸውን ዝርያዎች አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ እንዲሆኑ የመስራች ዘር የማባዛት ሥራ እያካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲናና አርሶ አደሮች በኩታገጠም አሰራር እየተባዛ ያሚገኘውና አርሶ አደሩ ልምድ እንዲለዋወጥ ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀው የመስክ ምልከታ የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።

በማዕከሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ አቶ ባያታ ጋዲሳ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በምርምር የሚያወጣቸው የሰብል ዝርያዎች ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።


 

ዝርያዎቹ በስፋት ተጠቃሚው አርሶ አደር ጋር እንዲደርሱ በምርምር ማዕከሉና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በማባዛት ተደራሽ እንደሚደረጉ አክሏል።

አቶ ባያታ እንዳሉት፤ ማዕከሉ በአሁኑ የመኽር ወቅት በምዕራብ አርሲና በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ከ150 ሄክታር በሚበልጡ የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በቅርቡ ከማዕከሉ የተለቀቁ ዝርያዎችን እያባዛ መሆኑን አስረድተዋል።

እየተባዙ ከሚገኙ ዝርያዎች መካከል በአንድ ሄክታር መሬት እስከ 72 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ''ቦኩ'' የሚባል ስያሜ የተሰጠው የስንዴ ዝርያ እንደሚገኝበት አመልክተዋል፡፡


 

የመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት፤ ማዕከሉ በአካባቢያቸው በመኖሩ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን በየጊዜው በማግኘት ምርታማነታቸውና ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል እስከ አሁን 116 የሚሆኑ የሰብል፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች ላይ ያተኮሩ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ ለተጠቃሚው ማሰራጨቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም