ክልሉ የሳይንስ እና ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች በመደገፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ የሳይንስ እና ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች በመደገፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እያደረገ ነው
አሶሳ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሳይንስ እና ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን በመደገፍ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው "የተማሪዎች የሳይንስ እና ፈጠራ ሥራ ለልማታችን እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም ለማሣደግ ያለመ የምክክር መድረክ በአሶሳ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በተማሪዎች የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት እና የተቋማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሐመድ ኡስማን እንደገለፁት፣በሀገር ደረጃ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሳደግ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት ራሳቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያለማምዱበት ዕድል እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በክልሉ በርካታ ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ቢሮው የፈጠራ ክህሎት ላላቸው ተማሪዎች የተለያዩ መድረኮችን በማመቻቸት ስራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተማሪዎች የፈጠራ ውድድር አሸናፊ ከነበሩት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ብርሃኑ ሲሳይን እንደ ማሳያ ያነሱት አቶ ሙሐመድ፤ ሌሎች ተማሪዎችም ያላቸውን ተሰጥኦ እና ችሎታ በመጠቀም በሁሉም ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
ተማሪ ብርሃኑ ሲሳይ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ሞተር መሥራቱን በማስታወስ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው ፊሊጶስ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በዲጂታል 2030 ያለመችውን ዕቅድ ለማሣካት ከትምህርት ቤት ጀምሮ በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ተማሪዎች ትልቅ ሀገራዊ ራዕይ ይዘው እንዲያድጉ እና የፈጠራ አቅሞቻቸውን አውጥተው ችግር ፈቺ ሥራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል የድጋፍና ክትትል ሥራ ከባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የፈጠራ ስራዎቻቸውን ላቀረቡ ተማሪዎች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።