ቀጥታ፡

አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታ ገጠም በማልማት ምርታማነታቸው አድጓል

ወላይታ ሶዶ ፤ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ):- በኩታ ገጠም  ስንዴን በክላስተር አልምተው ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን በጋሞ ዞን የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ አርሶ  አደሮች ተናገሩ።  

መንግስት በምግብ ራስን በመቻል ከተረጂነት ለመውጣት ለስንዴ ልማት ምርታማነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በጋሞ ዞን የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ የዶኮ ሻሌ የቀበሌ አርሶ አደሮች እንደገለፁት፤ በተናጠል ስናባክነው የነበረውን ጊዜና ጉልበት በኩታ ገጠም እንዲያብር በማድረግ ምርታማነታችንን አሳድገናል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አርሶ አደር ኤልያስ ባለው እንደገለጹት ከዚህ ቀደም መስመሩን ጠብቀው በኩታ ገጠም የማልማት ልምድ ስላልነበራቸው በብተና ዘርተው የሚያገኙት ምርት ጥቂት ነበር።

አሁን ግን በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ-ዘዴ በባለሙያዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ስንዴን በክላስተር አልምተው ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

አምና በተመሳሳይ ወቅት አንድ ሺህ 200 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን አንስተው ዘንድሮ ስራውን በማስፋትና በማዘመን ከተዘራው 30 ሄክታር ማሳ ከ1 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ሙላቱ ማስጌ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በተናጠል እያመረቱ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ነገር ግን በግብርና ባለሙያዎች በተደረገ ሙያዊ ድጋፍ እና ምክር ከአምና ጀምሮ በኩታ ገጠም ማልማት መጀመራቸውን ጠቁመው ይህም የጊዜ፣ የጉልበትና የግብዓት ብክነትን እንዳስቀረላቸው ገልጸዋል።

በኩታ ገጠም ማልማት ከጀመሩ ወዲህ በአብሮነት በትብብር የመስራት ባህላቸውን እንዳሳደገላቸውም ተናግረዋል።

መንግስት ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ  በተለይ ለኩታ ገጠም እርሻ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በወረዳው በአንድ ሺህ 700 ሄክታር ማሳ ላይ ስንዴ፣ ገብስና ሌሎች ሰብሎች እየለሙ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በጋሞ ዞን የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይስማ ከተማ ናቸው።

አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂና በግብዓት በመደገፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኩታ ገጠም ከለማው የስንዴ ልማትም 24 ሺህ 500 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዞኑ ያለው እምቅ የግብርና አቅም በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ-ዘዴና በቴክኖሎጂ በመደግፍ እየለማ መሆኑን  ገልጸዋል።

በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ከ490 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬዎች ተሸፍኖ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በክላስተርና በሜካናይዜሽን ለማልማት የግብዓትና የባለሞያዎች ድጋፍ መጠናከሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም