ቀጥታ፡

ለጂንካ ከተማ የኮሪደር ልማት ስኬታማነት ነዋሪዎች የድርሻቸውን እየተወጡ ነው

ጂንካ፣ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፡-በጂንካ ከተማ ለተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ስኬታማነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለፁ። 

በከተማዋ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቆ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀምሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎችም በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻና ለሥራ ምቹ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከነዎሪዎች መካከል አቶ ንጋቱ ክብረት በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ማድረጉን ተናግረዋል።


 

በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በከተማዋ የሚገኙ አደባባዮችን ከማስዋብ ባለፈ የእግረኛ መንገዶችን ለእንቅስቃሴ ምቹ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል።

በአሁኑ ወቅት ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን  ገልጸው፣ ለልማቱ ስኬታማነት ትብብር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አቶ ዮሴፍ መላኩ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ዕድገት ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመው፣ ለሥራው ስኬታማነት ከይዞታቸው 1 ነጥብ 5 ሜትር መልቀቃቸውን ተናግረዋል። 


 

ከዚህ በተጨማሪ በቀጣይ በገንዘብና በዕውቀት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት።

በከተማው በመጀመሪያ ምዕራፍ ከ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱን የገለጹት ደግሞ የጂንካ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የመሰረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ፈለቀ ወርቁ  ናቸው።

የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ መንገድ፣ የመዝናኛ ፓርክ፣ የመንገድ አካፋይ እና የመንገድ ዳር መብራቶችን ጨምሮ መከናወኑንም አስረድተዋል።


 

በሁለተኛው ምዕራፍ ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራ ለማከናወን ወደተግባራዊ  ስራ  መገባቱን ገልጸዋል።

ለሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የወሰን ማስከበር ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ያመለከቱት አቶ ፈለቀ፣ በልማቱም  የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች፣ የመንገድ ዳርቻና አካፋይ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ጨምሮ የከተማዋን ገፅታ የሚለውጡ መሰል የልማት ሥራዎች ይክናወናሉ ብለዋል።

ከአዲስ አበባ በ755 ኪሎ ሜትር ላይ የምትገኘው የዕድሜ ባለፀጋዋ ጂንካ ከተማ ለዘመናት ያላገኘችውን የመልማት ዕድል ኮሪደር ልማትን ተከትሎ ፈጣን እድገት እየተመዘገበባት መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም