በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቃለለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቃለለ ነው
ጭሮ ፤ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ባህል እየሆነ የመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እያቃለለ መሆኑን በዞኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በቦኬና ኦዳ ቡልቱም ወረዳዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንዳቃለለላቸው ነው የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የሚናገሩት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የተደረገላቸው ድጋፍ በርካታ ችግሮቻቸውን አቃልሎላቸዋል።
በቦኬ ወረዳ ቦኬ ጥቃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅዬ ስለሺ እንዳሉት በመኖሪያ ቤታቸው እርጅናና መፈራረስ ለብርድና ዝናብ ሲጋለጡ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም ለጤናና ሌሎች ለማህበራዊ ችግሮች እንዳጋለጣቸው አስታውሰዋል።
ይህን ችግራቸውን የተረዱት የወረዳው የበጎ ፈቃደኞች ቤታቸውን በማደስ ከችግራቸው እንደገላገሉአቸው አስረድተዋል።
ከሶስት ልጆቻቸው ጋር በተጎሳቆለ ቤታቸው ለችግር ተጋልጠው ይኖሩ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ፌይሩዛ መሐመድ ናቸው።
አሁን ላይ ያረጀ ቤታቸው በአዲስ በመተካቱ ትኩረታቸውን ስራቸው ላይ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
በኦዳ ቡልቱም ወረዳ ሙዲ ኢረሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ ሱሌ በበኩላቸው የመንግስት አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር ባደረጉላቸው ድጋፍ ሁለት ክፍል አዲስ ቤት እንደተገነባላቸው ገልፀዋል።
የመኖሪያ ቤታቸው በመታደሱም እፎይታ እንደተሰማቸው ጠቁመዋል።
የቦኬ ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ሳሚያ መሐመድ እንዳሉት በወረዳው በዚህ ዓመት ህብረተሰቡን በማስተባበር 700 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና ጥገና ተደርጎላቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
የኦዳ ቡልቱም ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አዳነ ፀጋ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እና በሌሎችም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ ስራ ለመስራት መታቀዱን ገልፀዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን 15 ወረዳዎች እና አምስት ከተሞች በዚህ ዓመት በ72 የተለያዩ መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ገንዘብ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ተወካይ አቶ ጀማል አሊዪ ናቸው።
በዓመቱ ከ200 በላይ አዳዲስ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ለማከናወን ታቅዶ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ከ150 በላይ መከናወኑን ገልፀዋል።
የአቅመ ደካማ ህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ከ 6ሺህ 800 በላይ መኖሪያ ቤቶች በበጎ ፈቃደኞቹ መከናወኑንም አመልክተዋል።