የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ሥራዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላችን ሚና እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ሥራዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላችን ሚና እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ሥራዎችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰለጠነ ምክክር በማድረግ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አልሞ እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም ኮሚሽኑ ለዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚያስፈልጉ አጀንዳዎችንና ግብዓቶችን የመለየትና የማሰባሰብ ማጠናቀቂያ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዛቸውን ትልሞች ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ መምህራን ማኀበር ፕሬዝዳንት ድንቅዓለም ቶለሳ፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረትም በሃሳብ ላይ የተመሠረተ ምክክር በማካሄድ አለመግባባቶችን መፍትሔ የሚሰጥ ሁነኛ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበሩም የትምህርቱን ማህበረሰብና አባላቱን በማስተባበር ለሀገር የሚጠቅሙ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰለጠነ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ቀጣዩ ትውልድ ሰላማዊትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዲረከብ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የየካ ክፍለ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸኃፊ መጋቢ ግርማ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግቦች በየዕለቱ ከሚያከናወኗቸው ተግባራት ጋር የተሰናሰሉ በመሆናቸው ሀገርን በሚያጸኑ አጀንዳዎች ዙሪያ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግቦችና ቀሪ ሥራዎች ስኬት በነቃ ተሳትፎ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
በሰለጠነ የምክክር ሥርዓት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል ሶፊያ ዘውዴ ናቸው።
ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት ቀሪ ሥራዎች ላይ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንደሚቀጡ ገልጸዋል።