ለገና በዓል ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በተረጋጋና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት አስችሎናል--ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
ለገና በዓል ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በተረጋጋና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት አስችሎናል--ሸማቾች
ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 27/2018 (ኢዜአ):-ለገና በዓል ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በተረጋጋና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንዳስቻላቸው የሆሳዕና ከተማ ሸማቾች ተናገሩ።
የበዓል ገበያ ሲሸምቱ የነበሩት የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ለበዓል የሚሆን የምርት አቅርቦት ችግር ባለመኖሩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በተረጋጋ ሁኔታ ለመሸመት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በከተማው የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሪት ሳራ ጌታቸው ለበዓሉ ቅቤ ለመግዛት እንደመጡ ገልጸው የምርት አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ በመኖሩ አማርጠው እንዲገዙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
አቶ አሰፋ ለራጎ እና ወይዘሮ ትዕግስት ዮሐንስ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው በበዓል ገበያው ሁሉም የምርት አይነቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን ተናግረዋል።
በገበያው የእርድ እንስሳት አቅርቦቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ የእርድ ሰንጋ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡
በከተማው ከተቋቋሙ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላት ለበዓሉ የሚሆናቸውን ሽንኩርትን ጨምሮ ሌሎች የፍጆታ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ከመቅረባቸው በላይ የዋጋ ጭማሪ አለመኖር ምርቶችን በተረጋጋና በተመጣጣኝ ዋጋ ለመግዛት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
በመንግስት ገበያውን ለማረጋጋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለበዓሉ የሚሆን ፍጆታዎችን በተረጋጋ ሁኔታ ለመሸት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በከተማው በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለሸማቹ በቀጥታ ማቅረባቸውን የገለጹት አቶ ሀብታሙ ላጲሶ ናቸው።
የቅዳሜና እሁድ ገበያው ሻጩንና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ተጠቃሚ እንዳደረገና በዓሉን በማስመልከት የተደረገ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን ገልጸዋል።
ያመረቱትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ማቅረባቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ መሆኑንም አመልክተዋል።
ለገና በዓል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የሀድያ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተከተል ዶባሞ ናቸው።
በሆሳዕና ከተማ በሚገኙ 12 የቅዳሜና እሁድ የግብይት ማዕከላት ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች በበቂ መጠን መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ይህም አምራቹና ሸማቹን ማህበረሰብ በቀጥታ በማገናኘት ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የተረጋጋ ግብይት እንዲካሄድና ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እያስቻለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ለመከላከል ስኳርና ዘይት በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ መደረጉንም ተናግረዋል።