መፍትሔ አፍላቂ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
መፍትሔ አፍላቂ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ ወጣቶች
በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል አሰልጣኝ ወርቁ ፈንታሁን ከጓደኛው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ያለውን የዶሮ እርባታ ስራን ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ፈጥረዋል።
ዘመናዊ የዶሮ ማርቢያ ቤት(ኬጅ) ለመፍጠር ያነሳሳቸው በባህላዊ መንገድ የሚከናወነውን አሰራር ለማዘመን በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመናዊው የዶሮ ኬጅ በተወሰነ አካባቢ ላይ በርካታ ዶሮዎችን ለማርባትና ዶሮዎቹን በንጹህ እና ጤንነታቸው በተጠበቀ ቦታ ማርባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የሚገኘውን የእንቁላል ምርት ሳይሰበር በቀላሉ መሰብሰብ የሚቻልበትን እድልም ይፈጥራል ብለዋል።
በቀጣይም ቴክኖሎጂው ለዘርፉ ውጤታማነት ከሚኖረው ፋይዳ አንጻር የማስተዋወቅና በስፋት ተመርቶ ወደ ገበያ እንዲቀርብ እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
አካል ጉዳተኞችን በቀላሉ መመገብና ፈሳሽ ነገሮችን ማጠጣት የሚያስችል ሮቦት የሰራው ደግሞ በጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ የደረጃ አራት ተመራቂ ተማሪ ዳግም ጋርጠው ነው።
ሮቦቱ ያለምንም የሰው ንክኪ አካል ጉዳተኞች በቀላሉ በሚጠቀሙበት መልኩ የተሠራ ነው ብሏል።
ስራው ውጤታማ እንዲሆን ኮሌጁ የግብዓት፣ የሙያ እና ሌሎች ድጋፎች እንዳደረገለትም ተናግሯል።
በኮሌጁ የቴክኖሎጂ ልማትና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ምክትል ዲን ደሜ መርሻ በአሰልጣኞችና በሰልጣኞች ቅንጅት ውጤታማ የፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
የመኖ መፍጫ፣ የዘመናዊ ዶሮ ኬጅ እና የፕላስቲክ መፍጫና ማቀነባበሪያ እንዲሁም ፕላስቲኩን ወደ ተለያየ ምርት መቀየር የሚችሉ ማሽኖች በኮሌጁ ተሰርተው ጥቅም ላይ ከዋሉ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።
የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝና ፈጠራዎቹን የማስተዋወቅ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ባለሙያዎችን እንዲሁም ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያመነጩ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምታስገባቸውን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት፣ አዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በቴክኒክና ሙያ የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች በሀገር ልማት ላይ አበረታች ወጤት እያመጡ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ የክህሎት ማበልፀጊያ ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ያላቸውን ዜጎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።