ቀጥታ፡

ለገና በዓል የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም በቂ ዝግጅት ተደርጓል -የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018(ኢዜአ)፡-ለገና በዓል የኃይል መቆራረጥ  እንዳያጋጥም በቂ ዝግጅት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።  

ተቋሙ የገና እና የጥምቀት በዓላትን በማስመልከት ባከናወናቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። 

በአገልግሎቱ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ኦፕሬሽንና ኤክሰለንስ ዳይሬክተር አቶ ፈረድ አብዱሰላም በመግለጫቸው፤ ገናን ጨምሮ  በመጪዎቹ በዓላት የሚኖረውን ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ ታሳቢ በማድረግ የኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አገልግሎቱ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በመላው ሀገሪቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመካከለኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች ፍተሻና ጥገና አስቀድሞ መከናወኑን ገልጸዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ የትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግና የጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በበዓላቱ ወቅት በሚኖረው ከፍተኛ የኃይል አጠቃቀም ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛውም የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ የኦፕሬሽን ቡድን መዘጋጀቱንም አክለዋል።

ኅብረተሰቡ በበዓላት ወቅት የኃይል ጫናን ለመቀነስ ከፍተኛ ፍጆታ የሚጠይቁ ሥራዎችን የኃይል ፍላጎት በማይበዛበት ሰዓት ለአብነትም ከምሽቱ 4:00 ሰዓት በኋላ ቢያከናውኑ ተመራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማንኛውም የኃይል መቆራረጥ ሲያጋጥም ወይም የአገልግሎት ጥቆማ ለመስጠት ኅብረተሰቡ በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችል ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም