ቀጥታ፡

መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በትኩረት እየሠራ ነው - ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018(ኢዜአ)፡- መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ችግሮችን በምክክር የመፍታት ባህል እንዲዳብር በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

መንግሥት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልንና ውይይትን እንደመርህ በመውሰድ ለሀገር ዘላቂ ብልፅግና በትጋት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ መንግሥት ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በሀገር ውስጥና በቀጣናው የዘላቂ ሰላም ግንባታ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

ጠንካራ ሀገር የሚገነባው በሕዝቦች አብሮነትና በመመካከር እንደሆነ መንግሥት ጽኑ አቋም እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት የሚሞክሩ አካላት ከስህተታቸው ተመልሰው ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ እያቀረበ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ ክልሎች በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወት በመመለስ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በሕዝቦች መካከል መቀራረብ እንዲኖር፣ የጋራ ትርክት እንዲገነባና ሀገር በቀል የችግር መፍቻ ሥርዓቶች እንዲዳብሩ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

ይህም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ለሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሀገራዊ የብልፅግና እና የዕድገት ጉዞን ለማሳካት ሰላም ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለልማት መሳለጥ መንግሥት በትኩረት መሥራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም