በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ይለማል
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡
በክልሉ ከለውጡ ወዲህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ከአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ጋር በማቀናጀት በመሰራቱ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገቡ ተመላክቷል።
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በተከናወነባቸው አካባቢዎች የተራቆቱ መሬቶችን ወደ አረንጓዴነት መቀየር፣ የአካባቢን ሥነ-ምህዳር ወደ ቀድሞው መመለስ፣ የአፈር መከላትን መከላከልና የመሬት እርጥበትን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንደተቻለ ተገልጿል፡፡
ምርታማነታቸውን የቀነሱና ምርት መስጠት ያቆሙ ተዳፋት ቦታዎችን በጠረጴዛማ እርከን ሥራ እንዲያገግሙ በማድረግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርታማነት መቀየር መቻሉም ተጠቅሷል፡፡
በተፋሰስ ልማት ያገገመ መሬት ላይ በሥነ ሕይወታዊ ሥራ የእንስሳት መኖ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ዕፅዋት በመትከል የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲያድግ መደረጉም ተመላክቷል፡፡
በእስከሁኑ የልማት ሥራ የተገኙ ጥቅሞችን በዘላቂነት ለማሳደግ ዘንድሮም በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የተፈጥሮ ሀብትና ደን ልማት ዘርፍ ኃላፊ አበባየሁ በየነ ናቸው፡፡
አቶ አበባየሁ ለኢዜአ እንደገለፁት ዘንድሮ በክልሉ በ678 ንዑስ ተፋሰሶች 147ሺህ 335 ሄክታር መሬት በተቀናጀ ሥራ ይለማል።
ዘንድሮ ለማልማት የታቀደው ከአምናው አንጻር የስምንት በመቶ ብልጫ እንዳለውና በእነዚህ ቦታዎች የጥናት፣ የዲዛይንና የካርታ ሥራዎች አስቀድሞ መሰራቱን ተናግረዋል።
የልማት ሥራውን ለማሳካትም 788 ባለሙያዎች የክህሎት ማጎልበቻ ሥልጠና መውሰዳቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከጥር 1 እስከ 10 ባሉት ቀናት በይፋ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡