ቀጥታ፡

ምሁራን ያሰቡትን፣ የጻፉትን፣ ያስተማሩትን መኖር እንዳይችሉ የሚያደርጓቸውን እንቅፋቶች መግራት አለባቸው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ ምሁራን ያሰቡትን፣ የጻፉትን፣ ያስተማሩትን መኖር እንዳይችሉ የሚያደርጓቸውን እንቅፋቶች መግራት አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

እብሪተኝነት፣ ማን አህሎኝነትና ከእኔ ወዲያነት ለምሁራን አደገኛ መርዞች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጽሁፍ አቅርበዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ስሜታዊነት፣ አድሎአዊ እሳቤዎች፣ ጀመኝነትና ቡድንተኝነት፣ ርዕዮትና ቀኖናዊነት፣ የመረጃ ጎርፍና ጫጫታ እንዲሁም ትዕቢትና ማናለብኝነት እና ማን አህሎኝነት በምሁርነት ውስጥ ያሉ እንቅፋቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

እነዚህ ባህሪያት እንቅፋቶች መሆናቸውንና በእነዚህ ምክንያትም ምሁራን ያሰቡትን፣ የጻፉትን፣ ያስተማሩትን መኖር እንዳይችሉ እንደሚያደርጓቸውም አብራርተዋል።

መጠየቅ ማለት ለመማር በር መክፈት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተው፤ እያንዳንዱ ምሁር በእነዚህ ባህሪያት ራሱን እየፈተሸ ራሱን እያዳመጠ ሊገራቸው እና ሊያስተካክላቸው ይገባል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ ምሁራን፤ ቅድመ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ምሁራን፣ አብዮታውያን ምሁራን፣ ስደተኞቹ ምሁራን እና ተስፈኞቹ ምሁራን በሚል እንደሚመደቡ ገልጸዋል።

ከእነዚህ መካከል አብዮታውያን ምሁራን፣ ስደተኞቹ ምሁራን እና ተስፈኞቹ ምሁራን ባለፉት ሰባ አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሻራውን ያሳረፈባቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም