ኢትዮጵያ በ2023ዓ.ም አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ትሆናለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በ2023ዓ.ም አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ትሆናለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018(ኢዜአ)፡- በ2023ዓ.ም ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅትም እንደ መንግሥት በ2023ዓ.ም ኢትዮጵያ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት መሆን አለባት የሚል ራዕይ ሠንቀናል፤ ይህንም መቶ በመቶ እናሳካዋለን ሲሉ አሥረድተዋል።
በ2040 ዓ.ም ደግሞ በዓለም አርዓያ የሆነች ሀገር ትሆናለች ሲሉም አመላክተዋል።
ለዚህ ራዕይ መሳካት ሰብዓዊ ልዕልና፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና አፍሪካዊት ኃያል መሆን የሚሉ ሦስት ትልሞች መኖራቸውን አስገንዝበዋል።
የተሻገረና የተሳሰረ ምሁራዊ ሚና ለማበርከትም፤ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፣ ከራስ የተሻገረ ዓላማ መያዝ እንዲሁም በሞያ ማገልገል ብሎም ድልድይ መሆን አስፈላጊ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል።
አክለውም፤ ከነባሩ የሐሳብ አጥር እንውጣ፣ አዳዲስ ሐሳብ ለመፍጠር እንሂድ፣ ሐሳብ ድንበር ስለሌለው ከጎራ ከሰፈር ወጥተን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ እንሥራ ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
ተናብበን፣ ተሰናስለን፣ ተማምረን፣ በጋራ ቆመን ብንሠራ ልናመጣ የምንችለው ውጤት ትልቅ ነው ብለዋል።
በመልካምነትና በበጎ ኅሊና ተባብረን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና እናሸጋግራት ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገልጸዋል።