በአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ ከቤኒን ናይጄሪያ ከሞዛምቢክ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ ከቤኒን ናይጄሪያ ከሞዛምቢክ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ግብጽ ከቤኒን በአጋዲር ስታዲየም ከምሽት አንድ ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብጽ በምድብ ሁለት በሰባት ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን 16 ውስጥ ገብታለች።
ተጋጣሚዋ ቤኒን በምድብ አራት በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በምርጥ ሶስተኝነት ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።
አንጎላ እ.አ.አ በ2010 ባዘጋጀችው 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ግብጽ በአህመድ ኤልሞሃመዲ እና ኢማድ ሞታይብ ግቦች ቤኒንን 2 ለ 0 አሸንፋለች።
ቡድኖቹ በሁሉም ውድድሮች አራት ጊዜ ተገናኝተው ግብጽ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ቤኒን እ.አ.አ በ2019 ግብጽ ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ በመግባት በአህጉራዊ መድረክ የተሳትፎ ታሪኳ ምርጡን ውጤቷን አስመዝግባለች።
የምዕራብ አፍሪካዋ ቤኒን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ከሰባት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ግብጽ ጠንካራ ፈተና ይጠብቃታል።
በሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ናይጄሪያ ከሞዛምቢክ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በፌዝ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በምድብ ሶስት በዘጠኝ ነጥብ በመሪነት ጨርሳለች።
ሞዛምቢክ በምድብ ስድስት በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ መርጥ ሶስተኛ ሆና ጥሎ ማለፍ ገብታለች።
ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
አንጎላ እ.አ.አ በ2010 ባዘጋጀችው 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሶስት ተገናኝተው ናይጄሪያ ሞዛምቢክን 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ፒተር ኦደምዊንጌ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኦባፌሚ ማርቲንስ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በአፍሪካ ዋንጫ ለአራተኛ ጊዜ እየተሳተፈች የሚገኘው ሞዛምቢክ በእስከ አሁን ተሳትፎዎቿ ከምድቧ አልፋ አታውቅም።
የዛሬ ጨዋታዎች አሸናፊዎች በሩብ ፍጻሜው እርስ በእርስ ይገናኛሉ።