ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት በመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ መድን ከመቀሌ 70 እንደርታ ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መካከል ሶስት  ጊዜ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በ12ቱ ጨዋታዎች ላይ 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል። መድን በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ እስከ አሁን በሊጉ ያሸነፈው የጨዋታ ብዛት አንድ ብቻ ነው። አምስት ጊዜ ሲሸነፍ ስድስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 17 ጎሎችን አስተናግዷል።

መቀሌ 70 እንደርታ በስምንት ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

በሌላኛው መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባህር ዳር ከተማ እስከ አሁን በሊጉ 12 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን በሶስቱ ሲያሸንፍ  በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በ12ቱ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ጎሎችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል። 

ቡድኑ በ15 ነጥብ 13ተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች መካከል በአራቱ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ጥሏል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

ድሬዳዋ ከተማ በ16 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም