ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ከ64 ሺህ ሔክታር በሚልቅ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ ይከናወናል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018(ኢዜአ)፡- በያዝነው ዓመት በክልሉ ከ64 ሺህ ሔክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የጋምቤላ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

አሁን ላይም በተለያዩ ወረዳዎች የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን በቢሮው የተፈጥሮ ሐብት ልማት ጥበቃ አጠቃቀም ዳይሬክተር ኬት ቾል ዳክ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ስራው የሚከናወነው የተለዩ 101 ተፋሰሶች ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራው 75ሺህ ሰዎች እንደሚሳተፉ ጠቁመው፤ አሁን ላይ የግብርና ባለሙያዎች በየተፋሰሱ በመገኘት ሙያዊ እገዛ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ክልል 168 ተፋሰሶች መኖራቸውንና ከእነዚህ መካከል 50 ያህሉ ወደ ልማት መግባታቸውን አውስተው፤ በቀሪዎቹ ላይ የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ እና ልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የዘንድሮው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የሥልጠና፣ የተፋሰስ እና ቁሳቁስ ልየታ መከናወኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ምርትና ምርታማነት መጨመር መቻሉንና በዚህም የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማደጉን አንስተዋል።

በተጨማሪም የአፈር መሸርሸር መቀነሱን ብሎም የተራቆቱ መሬቶች መልማታቸውን አስታውቀዋል።

አሁን እየተከናወነ ባለው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራም ተጠቃሚነቱ የጋራ መሆኑን ካለፉት ዓመታት ሥራዎች በመገንዘብ ሕብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም