ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሦስት መሠረታዊ ሥራዎች ይጠበቅባቸዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሦስት መሠረታዊ ሥራዎች ይጠበቅባቸዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 27/2018 (ኢዜአ)፡- ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሦስት መሠረታዊ ሥራዎች እንደሚጠበቁባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ ሁሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መማር ማስተማር፣ መመርመር መመራመር እንዲሁም መፍጠንና መተግባር የተሰኙ ሦስት መሠረታዊ ሥራዎች እንደሚጠበቁባቸው አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የሐሳብ፣ የተቋም እና የባህል ስብራቶች እንደ ሀገር ተግዳሮቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የእነዚህ ድምር ስብራትም በሀገር ደረጃ ውድቀት እንደሚያስከትል በአጽንኦት ገልጸዋል።
አሁን ባለንበት ዘመን ዕድል እና አጣብቂኝ ተግዳሮት አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጋራ እውነት አለመፍጠር፣ ከሞፈርና ቀንበር አለመላቀቅ፣ ከልዩነትና ግጭት አለመውጣት እንዲሁም ከሥነ-ምኅዳር አጥር አለማለፍ ያልተሻገርናቸው ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህን ለመሻገርም፤ የተሻገረ ብሔራዊ ራዕይ፣ ገቢር ነቢብ የለውጥ ሂደት፣ የተባበረ የለውጥ ዐቅምና ኃይል ያስፈልገናል ሲሉ አብራርተዋል።
የተሻገረ ብሔራዊ ራዕይ ሲባልም ከትናንት መማር፣ ለመስዋዕትነት መዘጋጀት እና ለትውልድ መሥራት መሆኑን አብራርተዋል።