ካሜሮን ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገባች - ኢዜአ አማርኛ
ካሜሮን ደቡብ አፍሪካን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገባች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተጠባቂ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ካሜሮን ደቡብ አፍሪካን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ማምሻውን በአል- መዲና ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጁኒየር ቻማዱ በ34ኛው እና ክርስቲያን ኮፋኔ በ47ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ኤቪደንስ ማክጎፓ በ88ኛው ደቂቃ ለደቡብ አፍሪካ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው አዝናኝ እና ተመጣጣኝ ፋክክር ለመመልከት ተችሏል።
ድሉን ተከትሎ የአምስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ካሜሮን ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።
በሁለቱ ሀገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክ ካሜሮን በደቡብ አፍሪካ ላይ የመጀመሪያ ድሏን አስመዝግባለች።
ካሜሮን በሩብ ፍጻሜው ከሞሮኮ ጋር የምታደርገው ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ ነው።
አዘጋጇ ሞሮኮ ዛሬ ከታንዛንያ ጋር ባደረገችው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ 1 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብታለች።