ቀጥታ፡

አዘጋጇ ሞሮኮ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ሞሮኮ ታንዛንያን 1 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብራሂም ዲያዝ በ64ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎል ሀገሩን አሸናፊ አድርጓል።

ዲያዝ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ አራት ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን መምራት ጀምሯል።

የሞሮኮው ኢስማኤል ሳይባሪ በ15ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል በቪዲዮ በታገዘ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሯል።

በጨዋታው ላይ ሞሮኮ ብልጫ ወስዳ ተጫውታለች።

ውጤቱን ተከትሎ አዘጋጇ ሞሮኮ ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀለች ሶስተኛ ሀገር ሆናለች።

ሞሮኮ በሩብ ፍጻሜው ከደቡብ አፍሪካ እና ካሜሮን አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።

ምሽት አራት ሰዓት ላይ ደቡብ አፍሪካ ከካሜሮን በአል -መዲና ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም