ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለገና በዓል በቂ ምርት ቀርቧል

ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለገና በዓል በቂ ምርት በመቅረቡ ግብይቱን የተረጋጋ እንዳደረገው የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ታሪኩ አካሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉን ምክንያት በማድረግ በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር በቅንጅት ተሰርቷል፡፡


 

ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት የቁጥጥር ሥራ ከክልል እስከ ወረዳ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የፍጆታ ምርቶች በቅዳሜና እሁድ ገበያ እንዲቀርቡ የማመቻቸት ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው የግብርና ምርቶች ገበያ ትስስር የመፍጠር ተግባርም እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በተደረገው ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ምርት በበቂ ሁኔታ መቅረቡንና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት መኖሩን ገልጸዋል።


 

በክልሉ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰርካለም ወልደሰንበት ለበዓሉ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ወደ ገበያ መቅረባቸውን ተናግረዋል።


 

ወይዘሮ ሙሉወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በዘይት፣ እንቁላልና አንዳንድ ምርቶች ላይ ቀደም ሲል ከነበረው ዋጋ እስካሁን የተለየ ጭማሪ አለመኖሩን ገልጸው በመንግሥት የሚደረገው ክትትል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


 

አቶ ኢያሱ ኮብቴት የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው የእርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም