አሲዳማ አፈርን ማከሚያ አማራጮችን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሲዳማ አፈርን ማከሚያ አማራጮችን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤታማ ነው
ዲላ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ አሲዳማ አፈርን ማከሚያ አማራጮችን በማስፋት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተከናወነ ባለ ሥራ ውጤት መገኘቱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ ‹‹ኦሲ ማሳ›› በተሰኘ ምጥን ማዳበሪያ በታከመ 13 ነጥብ 5 ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት ላይ ለሰርቶ መሳያ በለማ የምግብ ገብስ ምልከታ ተካሂዷል።
በመስክ ምልከታው ኦሲ ማሳ ከኖራ በአማራጭነት አሲዳማ መሬትን በማከም የሰብል ምርታማነትን ለማረጋገጥ ማስቻሉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አዲሱ በዛብህ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በምርምር የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማውጣት በሰርቶ ማሳያ ወደ አርሶ አደሩ እያስፋፋ ነው።
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን ተቀብሎ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ቢያደርግም የአፈር አሲዳማነት በውጤታማነቱ ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።
ኖራንና የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅሞ አሲዳማ አፈርን ማከሚያ አማራጮችን በማስፋት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አንስተው፣ ለዚህም ኦሲ ማሳ ምጥን ማዳበሪያ አማራጭ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሲ ማሳ ምጥን ማዳበሪያን ጥራትና ዘላቂ ውጤታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ተደራሽነቱን ለማስፋት ትኩረት መደረጉን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሃብታሙ(ዶ/ር) ናቸው።
ይህም ግብርናን በማዘመን ሽግግር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ በየደረጃው ቅንጅታዊ አሰራሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።
የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሄኖክ ተስፋዬ በበኩላቸው ኦሲ ማሳ ምጥን ማዳበሪያ አሲዳማ አፈርን በማከም የሰብል ምርታማነትን ማረጋገጥ የሚስችል ነው ብለዋል።
ምጥን ማዳበሪያውን ባለፉት ሦስት ዓመታት በኩታ ገጠም የአርሶ አደር ማሳ ተሞክሮ ውጤታማነቱ በመረጋገጡ በአሁኑ ወቅት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቡሌ ወረዳ በሰብል ከተሸፈነው 12ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ከ3ሺህ 800 የሚልቀው በአሲዳማነት የተጠቃ በመሆኑ ምርታማነት ላይ ጫና መፍጠሩን ያነሱት ደግሞ የቡሌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበበ ሽፈራው ናቸው።
ችግሩን ለመፍታት ከተለያዩ የምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ የኦሲ ማሳ ምጥን ማዳበሪያ ችግሩን እያቃለለ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በ13 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑንና ወደ 140 ሄክታር በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።