በኮምቦልቻ ከተማ ለገና በዓል የሚሆኑ የእርድ በሬዎች ለገበያ እየቀረቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮምቦልቻ ከተማ ለገና በዓል የሚሆኑ የእርድ በሬዎች ለገበያ እየቀረቡ ነው
ባሀር ዳር፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ለገና በዓል የሚሆኑ የእርድ በሬዎች በበቂ ሁኔታ ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የእንስሳትና አሣ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ መሃመድ አሊ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ለእንስሳት ሃብት ልማት ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርም በሁለት ክላስተሮች 47 ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት በሬዎችን በማድለብ ለአካባቢው ገበያ፣ ለአዲስ አበባ እና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ለገና በዓልም በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች፣ ሌሎች ባለሃብቶችና ግለሰቦች የደለቡ 27ሺህ የሚደርሱ በሬዎችን ጨምሮ ከብቶች በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረባቸውን አስረድተዋል።
አንድን በሬ አድልቦ ለገበያ ለማቅረብ 90 ቀናት ይወስዳል ያሉት አቶ መሃመድ አሁን ለገና በዓል የቀረቡ በሬዎችም ባለፉት ሦስት ወራት የደለቡና ጥሩ የሥጋ አያያዝ ያላቸው ናቸው ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር፣ በማህበር በማደራጀት፣ ቦታ በመስጠትና ብድር በማመቻቸት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉ በዘርፉ እድገት እንዲመዘገብ ማድረጉን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ማህበራቱ አስፈላጊው ግብአት እንዲያገኙ በማድረግና የገበያ ትስስር በመፍጠር እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።
በኮምልቻ ከተማ የሚገኘው የነመሃመድ፣ መሪማና ጓደኛኞቻቸው የከብት ማድለብ ሽርክና ማህበር ሰብሳቢ ሙሃመድ ፈንታው እንደገለጸው፣ ለገና በዓል ያደለቧቸውን 16 በሬዎች ለአካባቢው ገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በሬዎቹን ለማድለብ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች ከመምረጥ ባለፈ ሳይንሱ በሚያዘው አሰራር መሰረት አደልበው ለበዓል ገበያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በከበት ማድለብ ሥራ እንደተሰማሩ የተናገረው አቤል ተሾመ በበኩሉ ሥራው አዋጭ መሆኑን ጥናት ካደረገ በኋላ የነበረውን የቅጥር ሥራ በመልቀቅ በእንስሳት ማድለብ ሥራ መሰማራቱን ተናግሯል።
በአሁኑ ወቅትም የደለቡ 20 በሬዎችን ለገና በዓል ገበያ ማቅረቡንና በሬዎቹ ከአካባቢው ገበያ ባለፈ ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን ገልጿል።
ከማድለብ ሥራው በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን ከማስተዳደር ባለፈ ቁጠባውን በማጠናከር ወደ ባለሃብትነት መሸጋገር የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት ጥያቄ በማቅረብ ምላሹን እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል።