ለበዓሉ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በዓልን በአቅማችን ለማሳለፍ ያስችለናል-ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
ለበዓሉ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በዓልን በአቅማችን ለማሳለፍ ያስችለናል-ሸማቾች
ገንዳ ውሃ ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ለገና በዓል የዕርድ እንስሳትና ሌሎች ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ ሁኔታ መቅረባቸው በዓሉን በአቅማቸው ልክ ሸምተው ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን ሸማቾች ገለጹ።
በዞኑ የኮኪት ከተማ ነዋሪው አቶ ቢያዝን ሻምበል፤ ለገና በዓል የዕርድ እንስሳት በበቂ ሁኔታ መቅረቡ ምርቶችን አማርጠን ለመግዛት ያስችለናል ብለዋል።
የመሸጫ ዋጋውም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያለው በመሆኑ በዓሉን ባለን አቅም ገዝተው በደስታ ለማሳለፍ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አዳነ ክፍሌ በበኩላቸው፤ የዚህ ዓመት የገና በዓል ገበያ በአቅርቦትና በዋጋ የተሻለ መሆኑን በገበያዎቹ ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የስጋ በሬ ነጋዴ የሆኑት አቶ አስማረ አያሌው እንዳሉት፤ ለገንዳውኃ ከተማና ለአካባቢው ነዋሪዎች አቅማቸው በሚፈቅደው ገዝተው እንዲጠቀሙ የእርድ ከብት በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርበዋል።
የደለበ በሬ በ110 ሺህ የሸጡ ሲሆን ዝቅተኛ ደግሞ ከ65ሺህ ብር ጀምሮ እየሸጡ እንደሚገኙና ህብረተሰቡም በቡድን በቡድን በመሆን በሬዎችን እየገዛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በገንዳ ውኃ ከተማና ኮኪት ከተማ አውራ ዶሮ እስከ 1ሺህ 200፣ እንቁላል 20 ብር፣ ፍየልና በግ ከ8ሺህ እስከ 25ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ኢዜአ ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት በሊሁን እንደገለጹት፤ ለገና በዓል ፍጆታ የሚውሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል።
ከ100 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ሁለት ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ ስኳርና ሌሎች የግብርና ምርቶች ለህብረተሰቡ እየተሰራጨ መሆኑንም አክለዋል።
ምርት በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትና ሌሎች ነጋዴዎች እንዲቀርብ ከማድረግ ባሻገር ያለአግባብ ዋጋ ጭማሬ እንዳይኖር ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።