ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለበዓል ምርት በበቂ ሁኔታ ቀርቧል

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ለገና በዓል ገበያ የእንስሳት እና የምግብ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን የአስተዳደሩ የንግድ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ የንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኑ ጠሃ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ለሚከበሩ በዓላት ሸማቾች የሚፈልጉት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችና የእርድ እንስሳት በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ቀርበዋል።

በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የተደራጁ ማህበራት የግብርና ምርቶች ለቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ማቅረባቸውን ጠቅሰው የምግብ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በከተማዋ በተዘጋጁ የንግድና ባዛር ዐውደ ርዕይ ምርቶችን ተደራሽ ማድረጋቸውን አንስተዋል።


 

በተጨማሪም ከተጎራባች ክልሎች ጋር በተፈጠሩ ትስስሮሽ የግብርና እና የእርድ እንስሳት በበቂ ደረጃ ለገበያ እንዲቀርቡ መደረጉን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አሚኑ ገለፃ በአላትን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ዋጋ በሸቀጦች ላይ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ከማስተማር በዘለለ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።

በበአላት እየተደረገ የሚገኘው ክትትልና ቁጥጥር መጠናከሩን ጠቅሰው በዘመቻው ህገ ወጥ ዋጋ በጨመሩ 15 ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ነዋሪዎችም  ለዘንድሮው የገና በአል የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ለበአላት በተዘጋጁ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።


 

ለበአላት በተዘጋጁት ገበያዎች  የሚፈልጉትን ምርት በሙሉ ከአንድ ስፍራ በመለስተኛ ቅናሽ እየሸመቱ መሆኑን በመግለፅ።

የኢዜአ ሪፖርተሮች በቀፊራ፣ በሰባተኛ፣ በአሸዋ ገበያዎች ተዘዋውረው ባደረጉት ቅኝት ለገና በአል በቂ የእርድ እንስሳት እና ዶሮዎች ለገበያ መቅረባቸውን ተመልክተዋል።

የከብቶች ዋጋም  ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ተመሳሳይ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም