የደሴ ከተማን የትራንስፖርት አገልግሎት የማዘመን ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ከተማን የትራንስፖርት አገልግሎት የማዘመን ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል
አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 26/2018 (ኢዜአ)፡- የደሴ ከተማን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የማዘመን ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊና አረንጓዴ ትራንስፖርትን ከታዳሽ ኃይል ጋር በማቀናጀትና የካርበን ልቀትን በመቀነስ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።
የአረንጓዴ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂዎች ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመወጣት እንደ አረንጓዴ ዐሻራና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማስፋፋት ያሉ ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።
በዛሬው እለትም የደሴ ከተማ አሥተዳደር የገዛቸውን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶቡሶች ተረክቧል።
የከተማዋን ነዋሪው የትራንስፖርት አቅርቦት ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ነስረዲን ኃይሌ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በተለያዩ አማራጮች የታክሲ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በመንግሥት ወጪ የተገዙ አምስት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶቡሶችን አሥተዳደሩ መረከቡን ገልጸዋል።
አውቶቡሶቹ ለነዳጅ ይወጣ የነበረውን ወጪ ከማስቀረት በተጓዳኝ የከተማውን የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለቸው አስታውቀዋል።
አውቶቡሶች በቅርቡ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ተመድበው አገልግሎት እንደሚሰጡም ጠቁመዋል።
በቀጣይም በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀም ሁኔታ ከአሥተዳደሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እየተጣጣመ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።