ቀጥታ፡

ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕል ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት መሠረት ነው 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ ሰላማዊ የፖለቲካ ባሕል ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬት ወሳኝ መሠረት መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመተባበር "ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለሰላማዊ ምርጫ" በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ምርጫ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከር ዋነኛው ምሰሶ ነው። 


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገር ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለሰላማዊ ምርጫ ሂደትም ቁልፍ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

በተለይ በምርጫ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የሀገርን አንድነትና የሕዝብን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል። 

ሰላማዊ ምርጫን ማረጋገጥ የመንግሥት ብቻ ተግባር ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶችና የመላውን ሕዝብ የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማጠናከር የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል። 

ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን ምክር ቤቱ አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም