በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 3 ሺህ 895 ቶን ዓሳ ተመርቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 3 ሺህ 895 ቶን ዓሳ ተመርቷል
አሶሳ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 3 ሺህ 895 ቶን ዓሳ መመረቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናው ሀገራት ከሚያስገኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ባለፈ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ወደ ተሻለ ደረጃ መቀየርና ጠብቆ ማቆየት የሚያስችል ትልቅ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ፈጥሯል።
ንጋት ሃይቅ ቀደም ሲል ደረቃማ የነበረውን አካባቢ ልምላሜና ውበት በማልበስ የአየር ንብረቱን ጠብቆ ከማቆየት ባሻገር የባህር ትራንስፖርት፣ የቱሪስት መዳረሻነት እና የዓሳ ልማት ዋነኞቹ ትሩፋቶቹ ናቸው።
በሃይቁ ላይ የተደራጁ ወጣቶች ዓሳን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ጭምር በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የዓሳ ሀብት ልማት ባለሙያ ቡሸን ፉፋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ 3 ሺህ 865 ቶን ዓሳ ለማምረት ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 3 ሺህ 895 ቶን ተመርቷል።
አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ65 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን ይህም በርካታ ወጣቶች በንጋት ሃይቅ ላይ በመደራጀት ወደ ስራ በመግባታቸው የተገኘ ነው ብለዋል።
የንጋት ሃይቅ በክልሉ አራት ወረዳዎችን አልፎ የተኛ በመሆኑ በሃይቁ ላይ በአጠቃላይ ከ80 በላይ የሚሆኑ ማህበራት የሚደራጅ መሆኑን አንስተው፤ በእስካሁኑ እንቅስቃሴ 35 ማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
ማህበራቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመው ዓሳን በጥራት እንዲያመርቱ እና ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማድረግ 12 ባለሃብቶችን ከማህበራቱ ጋር በማስተሳሰር የሞተር ጀልባዎችና ሌሎች መሳሪያዎችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም ምርታቸውን ከክልሉ አልፎ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉም ለማህበራቱ ጀልባ እና የዓሳ መረብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በማህበራቱ የሚነሱ የቁሳቁስ አቅርቦት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከንጋት ሃይቅ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ትላልቅ ወንዞችን እና አነስተኛ የመስኖ ግድቦች ላይ ወጣቶች ዓሳ በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 9 ሺህ 965 ቶን ዓሳ ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።