ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና አለው
ጅግጅጋ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነት ቁልፍ ሚናን የሚጫወት መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርአያስለሴ ገለጹ።
የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም 2ኛው ዙር "ፋይዳ ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሐሳብ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በጅግጅጋ ከተማ ተካሄዷል።
በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርአያስለሴ እንደገለጹት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነትም ቁልፍ ሚናን የሚጫወት ነው።
ዜጎች ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በመውሰድ የዜግነት መብታቸውን መጠቀም እንዳለባቸውም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፤ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለሀገር ዕድገት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው በክልሉ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እንዲወስድ ሃላፊው አሳስበዋል።
የዛሬው የሩጫ ውድድርም የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ሂደትን ከማነቃቃት ባለፈ በስፖርት ተወዳዳሪ ወጣቶችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል መሆኑን አንስተዋል።
በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሩ የክልሉ አመራሮች፣ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አትሌቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።