ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ህጋዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የማልማትና የመጠቀም መብት መንፈግ አይቻልም

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 26/2018(ኢዜአ)፦ በዓባይና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ የማልማትና የመጠቀም መብት መንፈግ አይቻልም ሲሉ ምሁራን ገለጹ። 

የዓባይ ወንዝን በተመለከተ የግብጽ ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት ትርክት የማይታሰብና ጊዜውን የማይመጥን እሳቤ ስለመሆኑም ምሁራኑ አንስተዋል።

በኢትዮጵያዊያን እውቀት፣ ሃብትና ጉልበት የተገነባውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ግብጽ በርካታ ጥረቶችን ማድረጓ ይታወቃል።


 

ይሁን እንጂ በመንግስት ጠንካራ አቋም የዲፕሎማሲ የበላይነትና የህዝቡ ብርቱ ጥረት የግብጽ ሴራ ከሽፎ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ሀይል ማመንጨቱ፣ የዓሳ ሃብት መገኛነቱና የቱሪዝም ሀብትነቱ በተግባር ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ታሪካዊ፣ ህጋዊ፣ መልክአ ምድራዊና ተፈጥሯዊ መብቷም የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ ሆኖ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን በዓባይና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊና ተፈጥሯዊ የማልማትና የመጠቀም መብት በፍፁም መንፈግ የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል የውሃ ገብ አካላት ተመራማሪ ምህረት ደናንቶ (ዶ/ር)፤ የትኛውም ሀገር የተፈጥሮ ሃብቱን የማልማትና የመጠቀም መብቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ገልጸዋል።


 

በመሆኑም ኢትዮጵያ ዓባይንና ሌሎችንም የውሃ ሃብቶቿን በአግባቡ የማልማትና የመጠቀም መብቷ የተጠበቀ መሆኑን አንስተው የግብጽ ጠቅልሎ የመያዝ የቅኝ ግዛት ትርክት በዚህ ዘመን የማይታሰብና ጊዜው ያለፈበት መሆኑን አስረድተዋል። 

ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን አልምታ ከመጠቀም ባለፈ የባህር በር ባለቤት መሆኗ የግድ መሆኑን አጽዕኖት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የመሆን መብት በሁሉም መመዘኛዎች ተገቢ መሆኑንና የህልውና ጉዳይም ጭምር በመሆኑ ምላሽ እስከምናገኝ የሁላችንም ሃላፊነትና የትውልዱ የቤት ስራ ሆኖ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የውሃ ሀብትና ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ቴዎድሮስ አሰፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በተለይም የውሃ ሀብቶቿን በማልማት ጥቅም ላይ የማዋልና በቀይ ባህር ላይ መውጫና መግቢያ የማግኘት ጥረቷ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በዚህ የልማት ጥረትና የመጠቀም መብት ላይ ግብጽ እንቅፋት ለመሆን ጥረት ማድረጓ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በዓባይና ቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ህጋዊና ተፈጥሯዊ  የማልማትና የመጠቀም መብት የግብፅ ጊዜው ያለፈበት የቅኝ ግዛት እሳቤ ሊያሰናክለው አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም